በሆሳዕና ለ1 ሺህ ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ዩኒፎርምና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በሆሳዕና ለ1 ሺህ ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ዩኒፎርምና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
ሆሳዕና፣ ጥቅምት 4/2013 (ኢዜአ) ብርቱ ተስፋ የተባለ የህጻናት መርጃ ማዕከል በሆሳዕና ከተማ ለሚገኙ አንድ ሺህ ለተቸህፃናት የደንብ ልብስና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የማዕከሉ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ወጣት መድህን ስዩም እንዳስታወቀው ማዕከሉ ዛሬ ድጋፍ ያደረገው ደንብ ለብስ ፣ 8 ሺህ ደብተርና 2 ሺህ እስክርቢቶ ነው።
ለእያንዳንዱ ተማሪ በነፍስ ወከፍ ስምንት ደብተርና ሁለት እስኪሪብቶ እንዲሁም የትምህርት ቤት ዩኒፎርም ዛሬ እንዲሰጣቸው ተደርጓል።
ለደንብ ልብሱና ለትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ማዕከሉ ከ380 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ወጣት መድህን ተናግሯል።
በማዕከሉ የተሰባሰቡ የከተማዋ ወጣቶች የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ የወገኖቻቸውን ችግር እየተጋሩ መሆኑን አያይዞ ገልጿል።
ማዕከሉ የራሱ ገቢ ባይኖረውም በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር ጎዳና ላይ የነበሩ ህጻናትን ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ፣ ወላጅ አልባ ህጻናትን ደግሞ በማዕከሉ እንዲጠለሉ በማድረግ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል ብሏል።
በድጋፍ አሰጣጡ ላይ የተገኙት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ሴቶች ፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፋጤ ጀማል በበኩላቸው ማዕከሉ ከጽህፈት ቤቱ ጋር በመተባበር ለችግር የተጋለጡ ህጻናትን በመለየትና በመደገፍ ዘርፈ ብዙ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ወደ ኋላ ለቀሩ 1 ሺህ ለችግር የተጋለጡ ተማሪዎች ዛሬ የተደረገው ድጋፍ የዚሁ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን አስታውቀዋል።
የትህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ከተደረገላቸው ህጻናት መካከል ህፃን ሳሙኤል አበበ ወላጅ በችግር ምክንያት የ6ኛ ክፍል ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዶ እንደነበር ጠቅሶ ማዕከሉ ከጎዳና ህይወት በማላቀቅ ትምህርቱን እንዲጀምር ድጋፍ ስላደረገለት መደሰቱን ተናግሯል።
በሆሳዕና ከተማ የአራዳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግሰት አሰፋ በበኩላቸው ወረርሽኙ ባሳደረባቸው ተጽዕኖ ለችግር መዳረጋቸውን ገልፀው ለልጃቸው የተደረገው ቁሳቁስ ትምህርቱን ለማስቀጠል ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል ።