ቀጥታ፡

የዓለም ባንክና ኢትዮጵያ የ15 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4/2013 (ኢዜአ) የዓለም ባንክ ለከተሞች ሴፍቲኔትና ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ የ15 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ስምምነት አደረገ።

ባንኩ ድጋፍ የሚያደርግበትን ስምምነት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴና በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና  የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኡስማን ዳዮን ተፈራርመዋል።

ድጋፉ በ83 ከተሞች የድሀ ድሀ ደረጃ የሚገኙ ዜጎች ሕይወት ለማሻሻል ለተቀረፀው ፕሮጀክት ይውላል።

ከከተሞቹ 72ቱ  ፕሮጀክቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚተገበርባቸው ናቸው።

በተጨማሪም ለወጣቶች ሥራ ፈጠራና የምግብ ዋስትና ተቋማት እንደሚጠናከሩበት ተገልጿል።

አቶ አህመድ በዚሁ ወቅት ባንኩ የኢትዮጵያ የልማት ዋነኛ አጋር በመሆን ላበረከተው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ድጋፉ በአነስተኛ የኑሮ ሁኔታ የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት ከመቀየር ባለፈ፤ ለወጣቶች አዳዲስ ሥራ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ሚስተር ዳዮን በበኩላቸው በድጋፉ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ስኬታማ እንዲሆኑና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ጥሪ አቅርበዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ከባንኩ በተገኘ ብድርና የኢትዮጵያ መንግሥት በመደበው በጀት ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አውስተዋል።

በዚህም ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ፣ የድሃ ድሃ ዜጎችን፤ በእድሜ የገፉ፣ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውና ተደራራቢ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን እንዲሁም ኑሮአቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።

ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች አብዛኛዎቹ ሴቶች መሆናቸው ጫናቸውን መቀነስ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የተካሄደው ፕሮጀክት ውጤታማ በመሆኑ ወደ 72 ከተሞች እንዲሰፋ በመንግሥት መወሰኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ስምምነቱ የድሃ ድሃ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ  በከተሞች  የሚስተዋሉ ማህበራዊ ችግሮችን ያቃልላል ነው ያሉት።

ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ የ400 ሚሊዮን ዶላር(15 ቢሊዮን ብር)ድጋፍና ከኢትዮጵያ መንግሥት በሚመደብ 150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሚከወን ነው።

ፕሮጀክቱ  በሁሉም ክልሎች 798 ሺህ 500 ዜጎች በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ተጠቃሚ  እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም