ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የደረሱ የአርሶ አደር ሰብሎችን ሰበሰበ

ደብረብርሃን፣ ጥቅምት 4/2013 (ኢዜአ) ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞችን በማስተባበር በቀወት ወረዳ የደረሱ የአርሶ አደር ሰብሎችን በመሰብሰብ የአንበጣ መንጋ የሚያደርሰውን ጉዳት የመከላከል ሥራ ማከናወኑን አስታወቀ።

በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር የማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አልማዝ አፈራ እንደገለጹት የሰብል ስብሰባው የበረሃ አንበጣ  የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ያለመ ነው።

አሁን ላይ በምሥራቅ አማራ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ የአንበጣ መንጋው እያደረሰ ያለውን የሰብል ውድመት በጋራ መከላከል ካልተቻለ የሚደርሰውን ጉዳት መገመት አይቻልም።

ዩኒቨርስቲው የዞን ሴክተር መሥሪያ ቤት ሠራተኞችን በማስተባበር በሰብል መሰብሰብ ሥራ ያሰማራው በሀገር ላይ የሚደርሰውን ችግር ከግምት ውስጥ ያስገባ ምላሽ ለመስጠት ነው ብለዋል።

በዚህም ከ360 በላይ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና የመንግሥት ሠራተኞች በጤፍ አጨዳ መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይም የአንበጣ መንጋውን በመከላከልና በአርሶ አደሩ ምርታማነት ማሳደግ ላይ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በጥናትና ምርምር የታገዘ ተግባር ለማከናወን  እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሠረት ኃይሌ በበኩላቸው የአንበጣ መንጋው በዞኑ ዘጠኝ ወረዳዎች የሚገኝ 11 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ተከስቷል።

ምንም እንኳ አርሶ አደሩንና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማስተባበር ለመከላከል ጥረት ቢደረግም የአንበጣ መንጋው ከቁጥጥር ውጭ በመሆኑ እስካሁን 746 ሔክታር መሬት ላይ የሚገኝ ሰብል ማውደሙን ተናግረዋል።

በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የአንበጣ መንጋ በአውሮፕላን ርጭት ለማጥፋት በቀወት ወረዳ የአውሮፕላን ማረፊያ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ከአንበጣ መከላከል ጎን ለጎንም የደረሱ ሰብሎችን ቀድሞ በመሰብሰብ አርሶ አደሩን መታደግ እንዲቻል ሁሉም ኅብረተሰብ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በሰብል ስብሰባው ከተሳተፉት መካከል ዶክተር ታምራት ቸሩ እንደገለጹት አርሶ አደሩ በብዙ ድካምና ልፋት ያለማው ሰብል በድንገት በመጣ የአንበጣ መንጋ መበላት የለበትም በሚል በአጨዳ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

የአንበጣ መንጋውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መሳተፍ አርሶአደሩን መታደግ ብቻ ሳይሆን ሀገርን ከአደጋ መጠበቅና መከላከል ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ከዞን ሴክተር መሥሪያቤት ተሳታፊዎች መካከል አቶ ጌታሁን ባንጃ በበኩላቸው አሁን ላይ የጀመሩትን የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ተግባር በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

በቀወት ወረዳ ሰይበረት ቀበሌ  ነዋሪ አርሶ አደር ሉሉ ሞላ በበኩላቸው የአንበጣ መንጋው ሦስት ጥማድ የማሽላ ሰብላቸውን ሙሉ በሙሉ እንዳወደመባቸው ገልጸዋል።

አሁን ላይ ሦስት ጥማድ ማሣ ላይ የዘሩት የጤፍ ሰብል በመንጋው ይወድምብኛል ብለው ተስፋ በቆረጡበት ወቅት የመንግሥት ሠራተኞች ያደረጉላቸው ትብብር ሕይወታቸውን እንደታደገላቸው እንደሚቆጥሩት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም