ቀጥታ፡

በትግራይ በ34 ሺህ ሄክታር ሰብል ማሳ ላይ የተከሰተ አንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው

መቐለ ጥቅምት 04/13 (ኢዜአ )በትግራይ ክልል በ34 ሺህ ሄክታር የሰብል ማሳ ላይ የተከሰተን የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የአንበጣ መከላከልና የገቢ ማሰባሰቢያ ግብር ኃይል አስታወቀ። 

በክልሉ የተከሰተ አንበጣ መንጋ ለመከላከል ድጋፍ ተጠይቋል።

የግብረኃይሉ አባል  አቶ ገብረእግዛብሄር አረጋዊ ለኢዜአ እንደገለጹት  የአንበጣ መንጋው በክልሉ በአራት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 45 ቀበሌዎች ተከስቷል ።

መንጋው በተከሰተባቸው ቀበሌዎች  በ32 ሺህ ሄክታር የማሽላ፣ ጤፍና ገብስ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል ።

እስካሁን 90 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በባህላዊና ዘመናዊ መንገድ መንጋውን ለመቆጣጠር ጥረት መደረጉን ገልጸዋል ።

መንጋውን በቀላሉ መቆጣጠር ባለመቻሉ በሰብል ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት መቀጠሉን ጠቅሰዋል።

"የአንበጣ መንጋ ክስተት በዚሁ የሚቆም ሳይሆን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በባለሙያ ትንበያ ተረጋግጣል" ብለዋል ።

የጀመረው መንጋውን የመከላከል ሂደት ውጤታማ እንዲሆን የአጋሮች ድጋፍ አስፈልጓል" ያሉት አቶ ገብረእግዛብሄር ግብረሀይሉ ተቋቁሞ ለመከላከሉ ስራ የሚሆን ገቢ እያሰባሰበ መሆኑን ተናግረዋል ።

የክልሉ ነዋሪዎች በተለይም ባለሀብቶች እንዲሁም በሀገርና በውጭ የሚኖሩ የልማት አጋሮች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል ።

የልማት አጋሮች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተ  የሂሳብ ቁጥር  1000012045755 ድጋፋቸውን ገቢ በእንዲያደርጉ አቶ ገብረእግዛብሄር አስታውቀዋል ።

የሞሃ ለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ ሰራተኞችና ማኔጅመንት አባላት 100 ሺህ ብር እንዲሁም  የትግራይ ባህል ማህበር ፅህፈት ቤት ሰራተኞች 15 ሺህ ብር በትላንትናው እለት ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል ።

የፌዴራል መንግሥት በደቡባዊ ትግራይ እና በምሥራቅ አማራ የአንበጣ መንጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት ማካሄድ መጀመሩን ገልፇል።

ያም ሆኖ ግን በደቡባዊ ትግራይ የኬሚካል ርጭቱ በሚካሄድበት ወቅት የአንበጣ መንጋው ያለበትን አካባቢ ትክክለኛ መረጃ ያለመስጠት እና የማደናገር ሙከራዎች ማጋጠማቸውን አመራሮቹ መግለፃቸውን በትላንትናው እለት መዘደባች ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም