ቀጥታ፡

ግለሰቦችም ሆነ ኩባንያዎች የሚያወጡት ወርሃዊ የጥሬ ገንዘብ ጣሪያ አልተነሳም- ብሔራዊ ባንክ

ጥቅምት 03/ 2013 (ኢዜአ) ግለሰቦችና ኩባንያዎች ከባንክ እንዲያወጡ የፈቀደውን ወርሃዊ የጥሬ ገንዘብ ጣሪያ አለማንሳቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታና የባንኩ የከረንሲ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ አበበ ሰንበቴ የአዲሱ የብር ኖቶች ለውጥን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ግለሰቦችም ሆነ ኩባንያዎች የሚያወጡት ወርሃዊ የጥሬ ገንዘብ ጣሪያ ተነስቷል የሚለው መረጃ ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ለግለሰብ በቀን 200 ሺህ ብር ለኩባንያዎች ደግሞ እስከ 300 ሺህ ብር የሚደርስ ጥሬ ገንዘብ ከባንክ ማውጣት እንደሚፈቀድ አስታውቀዋል።

ይህ ማለት ደግሞ በወር የሚያወጡት የገንዘብ መጠን ለግለሰብ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር፤ ለኩባንያ ደግሞ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር መሆኑን አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ባለው አሰራር ግለሰብ በቀን የሚያወጣው የገንዘብ መጠን 50 ሺህ ብር፤ ለኩባንያ ደግሞ 75 ሺህ ብር ማውጣት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

በዚህ መሰረት ባንኩ በአጠቃላይ ለግለሰብም ሆነ ለኩባንያዎች የሚያወጡት የተቀመጠው ወርሃዊ የገንዘብ ጣሪያ መጠን አለመነሳቱን ኃላፊዎቹ አብራርተዋል።

ባንኩ በሶስት ወራት ውስጥ የብር ኖቶች ለውጥ ሥራውን ለማጠናቀቅ በያዘው ዕቅድ መሰረት ከ100ሺህ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ለውጥ ''በጥሩ መንገድ'' እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል።

የተጠቀሰው መጠን ገንዘብ በእጃቸው ያላቸው ሰዎች በቀሪዎቹ ጥቂት ቀናት በአፋጣኝ ወደ ባንክ ሄደው ገንዘቡን እንዲለውጡ አሳስበዋል።

ከኢምባሲዎች ጋር በተገናኘ የሰበሰቡትን ገንዘብ ምንጭ መረጃ ማቅረብ ከቻሉ፤ ገንዘቡን በአዲሱ የብር ኖቶች መለወጥ እንዲችሉ ውሳኔ መተላለፉን አስታውቀዋል።

የተከፈቱ የጋራ ሂሳብ ደብተሮችንም በተመለከተ የተቀመጠው 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ጣሪያ እነሱን እንደሚመለከት አስታውቀዋል። ከዚህ ውጭ ከተገኘ ሕገ ወጥ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አዲሶቹን የብር ኖቶችን አመሳስሎ ለመስራት የሞከሩ ሰዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ አሮጌው 100 ብር ከአዲሱ 10 ብር ጋር በቀለም ተመሳሳይነት እያጭበረበሩ ያሉ አካላት ስለመኖራቸው አንዳንድ መረጃዎች መውጣታቸውን ጠቅሰው፣ ለዚህም ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

ህብረተሰቡ በኖቶቹ ለውጥ ላይ በተለያዩ ቋንቋዎች ግንዛቤ እንዲኖረው እየተደረገ መሆኑን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።

አዲሱን 100 ብር በአሮጌው 130 ብርና ከዚያ በላይ የሚሸጡ አንዳንድ ሰዎች መኖራቸውን በመረጃ እንደተደረሰበት የተናገሩት ምክትል ገዥው፣ ህብረተሰቡ ተመሳሳይ ነገር ሲመለከት ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በአጠቃላይ እስካሁን ባለው የብር ኖቶችን ቅየራ የተዋጣ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በመላ አገሪቱ 6ሺ 561 የባንክ ቅርንጫፎች ላይ ገንዘቡ ስርጭት መደረጉንና በባንኮቹ ወደ 90 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገደማ መሰራጨቱን ተጠቅሷል።

በባንኮቹ 273 ሺህ አዳዲስ አካውንቶች ስለመከፈታቸውና በዚህም ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ መቀመጡ ተገልጿል።

ከባንኮች እስካሁን 140 ቢሊየን ብር ያህል መሰብሰቡንና 57 ቢሊዮን ብር ያልተሰበሰቡ አሮጌው የብር ኖቶች እንደሚቀሩ ተነግሯል።

በ5ሺህ 308 ኤቲኤም መክፈያ ማሽኖች አዲሱን የብር ኖት ማንበብ እንደተደረጉ አብራርተዋል።

ህብረተሰቡም ኖቶቹን ለመቀየር በቀረው ጊዜ ሳይዘናጋ የቀድሞዎቹን የብር ኖቶች እንዲቀይር ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም