መንግሥት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 80 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል -ሚኒስትር አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 80 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል -ሚኒስትር አህመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2013(ኢዜአ) መንግሥት በ2013 የመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት 80 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ አስታወቁ።
በኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት በሁለት አሃዝ እያደገ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀምን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የኮሮና ቫይረስን ተጽዕኖ በመቋቋም ዕድገት አስመዝግቧል።
ለግል የፋይናንስ ተቋማት በቢሊዬኖች የሚቆጠር ገንዘብ ፈሰስ በማድረግ እንዲሁም ከታክስና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያለውን አሰራር በማሻሻል የውጭ ንግዱንና ኢኮኖሚው ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም መሰረት ባለፉት ሶስት ወራት ከታክስ፣ ታከስ ካልሆኑ ገቢዎችና ከእርዳታና ብድር 80 ነጥብ 8 ገቢው መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
ከዚህም ባለፈ ለፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ለክልሎች ድጎማ 97 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመመስረቷ 474 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ግኝት እንዲሁም 465 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ፍሰት አስመዝግባለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር በመሰረተችው ወዳጅነት ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከጀርመን 117 እንዲሁም ከጃፓን 13 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አግኝታለች ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል ይውል ዘንድ የ 60 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ስጋት እየሆነ የመጣው በሁለት አሀዝ እያደገ የመጣው የዋጋ ግሽበት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑ የዋጋ ግሽበትን በመከላከል የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ማድረጉን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ተጨማሪ የዋጋ ግሽበት እንዳይፈጠር የጋራ ርብርብ ማድረግ ይጠይቃል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
በተጨማሪም መንግሥት የተቀናጀ የፊስካልና ሞኒተሪ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በአጽንኦት ይሰራል ብለዋል።
የመስከረም ወር የዋጋ ግሽበት ከነሐሴ ወር መቀነሱን ሚኒስትሩ አመልክተዋል።