ቀጥታ፡

በአሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሽቦ ሕይወት ላይ ያተኮረው መጽሐፍ በዚህ ሳምንት ይመረቃል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2013(ኢዜአ) በታዋቂው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሽቦ ሕይወት ላይ ያተኮረው መጽሐፍ የፊታችን ቅዳሜ ይመረቃል።

"አዳኙ አሰልጣኝ " የተሰኘው መጽሐፍ በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ነው። 

አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሽቦ ''በልጅነቴ አሰልጣኝነትን እጠላው ነበር'' ይላሉ። ''አሰልጣኝነትን የምጠላው ግን ሙያውን ሳይሆን፤ አሰልጣኞች ሲመሰገኑ ሳይሆን ሁሌ ሲወቀሱ እስማ ስለነበር ያንን መጥፎ ስም በመፍራት ነበር'' በማለት ያኔ ምክንያታቸውን ያቀርባሉ።

የስምንተኛ ክፍል ተማሪ በነበሩበት ጊዜ በአትሌቲክስ ስፖርት ይወዳደሩ እንደነበረ የሚገልጹት አሰልጣኙ፣ በተለይ በውትድርና ከተቀጠሩ በኋላ ለአትሌቲክስ ያላቸው ፍቅር ጨምሮ አሰልጣኝነት መተዳደሪያቸው  መሆን መጀመሩን ያወጋሉ።

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አትሌቲክስ ቡድን በማሰልጠን ሥራ የጀመሩት ኮማንደር አሰልጣኝ ሁሴን፣የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን በ1985 ለባርሴሎና ኦሎምፒክ በነበረው ዝግጅት የዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ምክትል በመሆን ማሰልጠን ጀመርኩ ይላሉ።

ኮማንደር አሰልጣኝ ሁሴን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የብሔራዊ ቡድኑ ምክትልና ዋና አሰልጣኝ በመሆን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በታላላቅ የውድድር መድረኮች ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ካደረጉ አሰልጣኞች አንዱ ለመሆን ችለዋል።

አሰልጣኝ ሁሴን ሶስት አሥርታት በተጠጋው አገልግሎታቸው ከ70 በላይ አገሮችን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ተጉዘዋል።

በአገር ውስጥና ውጭ ውድድሮች ያገኙትን ልምድና በዘርፉ ያካበቱትን ዕውቀት ለተተኪ አሰልጣኞችና አትሌቶች ለማሸጋገር ''አዳኙ አሰልጣኝ’’ በሚል ርዕስ መጽሐፍ አበርክተዋል።

መጽሐፉ የአሰልጣኙ ሕይወት ታሪክና አሰልጣኞች መከተል የሚገባቸውን የስልጠና መርሆዎች ''በሰፊው'' ያትታል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ስፖርትና የአትሌቶች አመጋገብ፣ አትሌቶች ስኬታማ ለመሆን መከተል የሚገባቸው ሥነ- ምግባርና አበረታች መድኃኒት የሚጠየፉ አትሌቶች ለማፍራት ያለሙ ዝርዝር ጉዳዮች እንደተካተቱበት  ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ መጽሐፉ ለአትሌቲክሱ ዕድገት አስተዋጽኦ አለው ትላለች።

መጽሐፉ በአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች ለሚገኙ የስፖርት ቤተሰቦች በፌደሬሸኑ በኩል ተደራሽ እንደሚደረግ አረጋግጣለች።

በዓቢይ ፈቅይበሉ አዘጋጅነት የተጻፈው "አዳኙ አሰልጣኝ "የተሰኘው መጽሐፍ በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቷል።በቀጣይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንደሚቀርብ ታውቋል።

መጽሐፉ በአማርኛው 337 ገጾች ያሉት ሲሆን፣ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የተዘጋጀው ደግሞ 420 ገጾች አሉት።

በመጽሐፉ ምረቃ ሥነ ሥርዓት የየመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አትሌቶችና አርቲስቶች በተገኙበት ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም