ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ከመነጠል ተግባሩ ሊታቀብ ይገባል -- የትግራይ ተወላጆች - ኢዜአ አማርኛ
ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ከመነጠል ተግባሩ ሊታቀብ ይገባል -- የትግራይ ተወላጆች
አዲስ አበባ ጥቅምት 3/2013 (ኢዜአ) ህወሓት በትግራይ ሕዝብ ስም ከመነገድና ከኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ከመነጠል ተግባሩ መታቀብ ይኖርበታል ሲሉ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ከተማ የጉለሌ ክፍለ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ተወላጆች አባላት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የህወሓት አመራሮች የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ መስዋዕትነት ያመጣውን ድል ለራሳቸው ጥቅም ተጠቅመውበታል ነው ያሉት።
በአገሪቷ የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ እየሰሩ በመሆኑ ከዚህ ድርጊታቸው መታቀብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
በአመራሮቹ ተግባርና የትግራይ ሕዝብና ህወሓት አንድ ናቸው በማለት በሚነዙት አሉባልታ የትግራይ ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲታይ እየተደረገ እንደሆነም ገልፀዋል።
የትግራይ ሕዝብ ይህን እኩይ ተግባራቸውን መረዳት አለበት ሲሉም አመልክተዋል።
ህወሓት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በሙስናና ብልሹ አሰራር መዘፈቁንና ይህም ከመጣበት ዓላማ ውጭ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የትግራይ ሕዝብ ሃሳቡን በነጻነት እንዳይገልጽ ታፍኗል፣ ጊዜ ጠብቆ ግን የሕዝቡ ቁጣ መፈንዳቱ አይቀርም ነው ያሉት ተወላጆቹ።
ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የትግራ ተወላጆች በህወሓት ፕሮፓጋንዳ እየተሳሳቱና ስጋት ውስጥ እየገቡ በመሆኑ የማንቃት ስራ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠላም ፈላጊ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በሁሉም ቦታ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በትክክለኛው መንገድ በመደራጀት ብልጽግናን እንዲቀላቀሉ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ጠላቶቹን በጋራ የሚያሳፍረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠልና የፖለቲካ ልዩነትን በውይይት መፍታት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍሰሃ ጥበቡ በበኩላቸው ብልጽግና ሁሉንም ሕዝቦች በአንድነት ወደ ብልጽግና የሚውስድ ድርጅት ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በአገሪቷ ባለው ለውጥ ሁሉንም ሕዝቦች በአንድነት የሚያስተናግድ ስርዓት መመቻቸቱንም ጠቁመዋል።
ወደ ስልጣን መምጣትን በምርጫ ካርድ ብቻ መወሰን የሚያስችል ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑንም ገልፀዋል።