ድህረ አደጋ ምላሽን መሰረት ያደረገው የአደጋ መከላከል ስራ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ድህረ አደጋ ምላሽን መሰረት ያደረገው የአደጋ መከላከል ስራ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋት ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 3/2013(ኢዜአ) የአደጋ መከላከል ትኩረቱ ድህረ አደጋ ምላሽ ላይ ያጠነጠነ መሆኑ ኢትዮጵያን ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ እንድታወጣ እየዳረጋት መሆኑ ተገለፀ።
የአደጋ ስጋት አስተዳደር ፖሊሲና ስትራቴጂ እየጨመሩ ካሉ የአደጋ አይነቶች ጋር የተጣጣመ ሊሆን ይገባልም ተብሏል።
32ኛው ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀን በኢትዮጵያ ለ11ኛ ጊዜ "የተጠናከረ የአደጋ አስተዳደር ለሕዝብ ልማትና ዕድገት" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በበይነ መረብ በተካሄደ ውይይት ተከብሯል።
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ስጋትና መልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አቶ አብርሃም አበበ ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ትኩረት አደጋን ቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
የቅድመ መከላከል ስራ አደጋ ከደረሰ በኋላ የሚመጣውን ጉዳት የሚቀንስ በመሆኑ አገራት ትኩረታቸውን በዚሁ ላይ ማድረግ እንዳለባቸው ይመከራል ነው ያሉት።
ይሁንና በኢትዮጵያ የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ አደጋ ከደረሰ በኋላ የሚደረግ ድጋፍ ላይ ያተኮረ በመሆኑ አገሪቷን ለብዙ ወጪ እየዳረጋት መሆኑን ተናግረዋል።
ከድህረ አደጋ ምላሽ በመውጣት የቅደመ አደጋ ማስጠንቀቂያ ስርዓት በመዘርጋት የሚወጣውን ወጪ መቀነስ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጠናከረ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ስርዓት ውስጥ አደጋን ቀድሞ መከላከል ዋነኛው ጉዳይ እንደሆነና የልማት አጋሮቹም በዚሁ ላይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የአደጋ ስጋት ቅነሳን አስመልክቶ ኢትዮጵያ እ.አ.አ 2015 በጃፓን ሴንዳይ ከተማ የተፈረመውን የሴንዳይ የአደጋ ስጋት ቅነሳ የትብብር ማዕቀፍ ተቀብላ እ.አ.አ ከ2016 ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገች ነው።
እንደ አቶ አብርሃም ገለጻ በማዕቀፉ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ወቅቱን የሚመጥን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስትራቴጂ ፖሊሲ መኖር ነው።
ኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ፖሊሲና ስትራቴጂ ቢኖራትም ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ከማጣጣም አኳያ ድክመቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ችግሩን ለመፍታት ክልሎችና ከተማ አስተዳሮች ፖሊሲና ስትራቴጂውን ካሉበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር አስተሳስረው እንዲጠቀሙ ለማድረግ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።
ክልሎችና ከተማ አስተዳሮች በአደጋ ምላሽ ያላቸውን አቅም ለማጎልበት ኮሚሽኑ ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን የቴክኒክ ድጋፎችን እያደረገ ነው ብለዋል።
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የቅደመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ ነግዬ ኃይሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቅድመ አደጋ መቆጣጠር ላይ ያላት አቅም እየተሻለ ቢመጣም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በቴክኖሎጂና በእውቀት ላይ የተደገፈ የቅድመ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ስራ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራበት ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ጽህፈት ቤት የአፍሪካ ኅብረት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቲዎስ ሁንዴ እንዳሉት የቅድመ አደጋ ማስጠንቀቂያ በአደጋ ጊዜና ከአደጋ በኋላ ከሚከናወኑ ስራዎች ጋር በጥምረት መከናወን አለበት ብለዋል።
የአደጋ ስጋት አስተዳደር ፖሊሲና ስትራቴጂ እየጨመሩ ካሉ የአደጋ አይነቶች ጋር የተጣጠመ ሊሆን እንደሚገባና በየጊዜው ከሚፈጠሩ አዳዲስ ክስተቶች ጋር እኩል መሄድ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አደጋዎች ከደረሱ በኋላ ከሚሰሩ ስራዎች የቅድመ አደጋ ማስጠንቀቂያ ስርዓት በመዘርጋት የአደጋ ስጋት መቀነስ ወደሚያስችለው ምዕራፍ ለመሸጋገር መልካም ጅምሮችን እያሳየች ነው ብለዋል።
ጽህፈት ቤቱ ኢትዮጵያ ለምታደርገው የአደጋ ምላሽ አሰጣጥና ሌሎች የአደጋ ስጋት አስተዳደር ስራዎች የሚያደርገውን የቴክኒክ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀንን አስመልክቶ በተካሄደው የበይነ መረብ ውይይት የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በኢትዮጵያ በድርቅ፣ በጎርፍ፣ በግጭት፣ በአንበጣና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት 15 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።