ቀጥታ፡

በማእከላዊ ጎንደር የጭልጋ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ እየተካሔደ ነው

ጎንደር፣ ጥቅምት 3/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በማእከላዊ ጎንደር ዞን ከ386 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የጭልጋ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የሰሜን ምእራብ ሪጅን የትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ኦፕሬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ውበት አቤ ለኢዜአ እንደተናገሩት የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ 5 ከተሞችን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማሻሻል የሚያግዝ ነው፡፡

በሃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ተጠቃሚ ከሚሆኑት ከተሞች መካከልም ጭልጋ፣ ደልጊ፣ ነጋዴ ባህር፣ ሳንጃና የትክል ድንጋይ ከተሞች ይገኙበታል ።

የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያው መገንባት በከተሞቹ የሚታየውን የሃይል እጥረትና ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር በከፍተኛ ደረጃ የሚፈታ ነው ብለዋል ፡፡

በተጨማሪም ለከተሞቹ የሃይል ፍላጎት ጥያቄ የተሟላ ምላሽ ለመስጠት ከማስቻሉም ባለፈ ለሚካሄዱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ ያግዛል፡፡

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ለታቀፈችው የጎርጎራ ከተማም ወደፊት አማራጭ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ የሚያስችል ፕሮጀክት እንደሆነም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡   

ጣቢያው 25 ሜጋ ቮልት የኤሌክትሪክ ሃይል የማሰራጨት አቅም ሲኖረው የሁለት ከፍተኛ ትራንስፎርመሮች ተከላ ስራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከአዘዞ ጭልጋ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የሃይል ማስተላላፊያ መስመር የብረት ምስሶ ተከላ ስራም በተመሳሳይ ተጀምሮ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡  

በ18 ወራት ውስጥ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ውል ተወስዶ የነበረ ቢሆንም ባለፈው አመት በአካባቢው በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት ግንባታው ዘግይቶ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በዚህ አመት መጨረሻ ግንባታውን በማጠናቀቅ ወደ አገልግሎት ለማስገባት በእቅድ እንደተያዘም አስረድተዋል፡፡

የአዘዞ ጭልጋ የከፍተኛ ሃይል ማስተላላፊያ መስመር ግንባታ ተቆጣጣሪ ኢንጂነር ሃብታሙ ሃይሉ በበኩላቸው 40 ኪሎ ሜትር የሸፈነ የከፍተኛ ሃይል ማስተላላፊያ የብረት ምሰሶዎች ለመትከል የሚያስችል ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

እስካሁንም የ35 የብረት ምሰሶዎች ተከላ ለማካሄድ የሚያስችል የኮንክሪት ስራ የተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ 50 ምሰሶዎች ተከላ ለማካሄድ የሚያስችል የጉድጓድ ቁፋሮም መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዘዞ ጭልጋ፣የፊንጫ ሻንቡ እና የመቱ ማሻ የሃይል ማስተላላፊያና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ዘለቀ በበኩላቸው ለአዘዞ ጭልጋ የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ የተመደበው በጀት በአለም ባንክና በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም