ቀጥታ፡

የመሬት ይዞታ ማረጋጋጫው የወሰን ይገባኛል ግጭትን እንዳስቀረላቸው በምዕራብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ

መተማ ግንቦት 5/2010 የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታቸው የመሬታቸውን ለምነት በመጠበቅ ይከሰት የነበረውን የወሰን ይገባኛል ግጭት እንዳስቀረላቸው በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ አርሶ አደር አቶ ጎባለ ጌጡ በመተማ ወረዳ የወዲ አምበሶ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ቀደም   ሲል በወሰን መገፋፋት ምክንያት ግጭት እየተነሳ የሰው ህይወት መጥፋትና ሌላም ጉዳት ይደርስ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ " የይዞታ ማረጋገጫ ደብተራችን ችግሩን በማስቀረት የተረጋጋ ኑሮ እንድንኖር አግዞናል"  ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደር አቶ ውበቱ ተረፈ በበኩላቸው ቀደም ሲል የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር ባለመኖሩ ምክንያት በመሬት ሃብታቸው ያለመተማመን ችግር እንዳነበረባቸው ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት የመሬቱን ደህንነት ጠብቀው ምርታማነትን ለማሳደግ እምብዛም ጥረት እንደማያደርጉ ጠቁመው  አሁን ግን በዙሪያው ያለውን የዛፍ ደን ከመጠበቅ ጨምሮ የመሬቱን ለምነት የሚያሳድጉ ተግባራትን እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በእርሻ ማሳቸው ላይ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ በመንከባከብና በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ተጨማሪ ዛፎችን ጭምር እየተከሉ መሆናቸውንም አውስተዋል። ቀደም ሲል የሴቶችንና የአቅመ ደካሞችን መሬት አንዳንድ ህገ-ወጥ ሰዎች ይቀሙ እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ የዳስ ቀበሌ አርሶ አደር ወይዘሮ አይናለም መብራቱ ናቸው፡፡ "ይህ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተሩ በህግ ተከራክረን  የምናሸንፍበት  ዋስትና ሆኖል"ብለዋል። በዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም የስራ ሂደት መሪ አቶ ወርቁ ዘውዱ በበኩላቸው በቋራ ፣ መተማና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች የመጀመሪያ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መስጠት በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም ከተመዘገቡት 70 ሺህ 471 የገጠር መሬት ባለይዞታዎች ወስጥ ለ53 ሺህ 445 የመጀመሪያ  ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ተሰጥቷል። በመተማ ወረዳ  አዲስ የመሬት ምዝገባ ባለመጠናቀቁና በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አንዳንድ ቀበሌዎች ከግንዛቤ እጥረት መሬቱን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸውን የደብተሩ አሰጣጥጡ መዘግየቱም ጠቅሰዋል። በዞኑ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ለአርሶ አደሮች የመስጠቱ ተግባር በተያዘው ዓመት ተጠናቆ የካዳስተር ( በአየር ላይ የሚነሳ ካርታ) ስራ  ይካሄዳል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም