ቀጥታ፡

የከተሞችን ቆሻሻ አወጋገድ ከአረንጓዴ ልማት ጋር ተቀናጅቶ እንዲተገበር እየተሰራ ነው

ባህርዳር፣ ጥቅምት 3/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ ከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድን ከአረንጓዴ ልማት ጋር ተቀናጅቶ እንዲተገበር እየተሰራ መሆኑን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ።

የዓለም የከተሞች ቀን ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ዴኤታው ዶክተር መስፍን አሰፋ እንደገለጹት ከተሞች በማስተር ፕላናቸው መሰረት 30 በመቶው ቦታቸውን ለአረንጓዴ ልማት እንዲያውሉ ህጉ ያስገድዳል።

በዚህ መሰረት ከተሞች ለኑሮ የሚመቹ፣ ሳቢና ማራኪ እንዲሆኑ የአረንጓዴ ልማት ቦታዎች ጠብቀው  እንዲያለሙ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዩ ኤን ዲፒ ጋር በመተባበር በአዳማ፣ ባህር ዳር፣ ቢሾፍቱ፣ ሐዋሳ፣ መቀሌና ድሬዳዋ ከተሞች የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ሸዶችን በመገንባት የሚወገደው ደረቅ ቆሻሻ ወደ ኮምፖዚትነት ተቀይሮ ለልማት እንዲውል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል ።

ሌሎች ከተሞችም ከዚህ ተሞክሮ ወስደው ደረቅ ቆሻሻን ከአረንጓዴ ልማት ጋር አቀናጅተው በመስራት ወደ ሃብትነት በመቀየር ለኑሮ አመቺ ሁኔታ መፍጠር አለባቸው ብለዋል ።

በዓለም ባንክ በጀት የሚደገፉ 117 ከተሞች በሚመደብላቸው በጀት የመሰረተ ልማት ስራዎችና የአረንጓዴ ልማት ቦታዎችን እንዲያለሙ የአቅም ግንባታ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የባህርዳር ከተማም ተፈጥሮ የሰጣትን ፀጋ በመጠቀም የአረንጓዴ ልማት ቦታዎችን በማስተር ፕላኗ መሰረት እየተገበረች የምትገኝ በመሆኗ ለሌሎች ከተሞች ልምድ የሚቀመርበት ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል ።

በቀጣይም ሁሉም ከተሞች የአረንጓዴ ልማት ቦታዎችን በማልማትና ቆሻሻን ወደ ሃብትነት በመለወጥ ለህብረተሰቡ ጥቅም እንዲያውሉ ይደረጋል ብለዋል ።

በተባበሩት መንግስታት የዩ ኤን ሃቢታት የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ አክሊሉ ፍቅረ ስላሴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የከተሞች እድገት ዘላቂ እንዲሆን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ተባብሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የተጀመሩ ድጋፎችም በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የደረቅ ቆሻሻ ቴክኒካል ባለሙያ አቶ ሰመረ ገብረፃድቅ ባቀረቡት ጽሁፍ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድን ማዘመን ለከተሞች ፅዳትና ለነዋሪዎች ደህነነት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በተለይ የደረቅ ቆሻሻን ወደ ኮምፖዚት መቀየር የጀመሩ ስድስት ከተሞች ከ9 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ወደ አረንጓዴ ፓርክነት በመቀየር ማልማት መቻላቸውን አስረድተዋል።

በአረንጓዴ ልማትና በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ በቀጣይ ተቋማዊ አደረጃጀትና አቅም ግንባታን ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም ጌታሁን በበኩላቸው በከተማዋ ከ300 የሚበልጡ የህዝብ አረንጓዴ ፓርኮች እየለሙ ይገኛሉ ብለዋል ።

ከተማዋ ውብና  ተፈጥሮ የቸራት በመሆኗ ለነዋሪዎቿ ምቹና የቱሪስትን ቀልብ የምትስብ  ለማድረግ በአስተዳደሩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

''ንፁህና አረንጓዴ ከተሞች ለዘላቂ ልማት'' በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም የከተሞች ቀን በባህር ዳር ከተማ ከትላንት ጀምሮ በጉብኝትና በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም