የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር መደበኛ ጉባኤውን በሐዋሳ ማካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር መደበኛ ጉባኤውን በሐዋሳ ማካሄድ ጀመረ
ሐዋሳ፣ ጥቅምት 3/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክር ቤት 33ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በሐዋሳ ማካሄድ ጀመረ፡፡
በመድረኩ የተገኙት በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ ባሰሙት ንግግር የመምህራን ማህበሩ የሃገሪቱን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚመራ ሰው የማፍራት ከፍተኛ ሃላፊነት ያለበት ነው ብለዋል፡፡
ሃገሪቱ እያካሔደች ላለው ልማትና ብልጽግና ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ያለ ማህበር መሆኑንም ተናግረዋል ።
ይሁን እንጂ ባለፉት ጊዜያት ምቹ መደላድል ባለመኖሩ ማህበሩ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ በተፈለገው ልክ አለማገልገሉን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ በሆነ መልኩ የተጣለበትን ሙያዊ ሃላፊነት እንዲወጣ ለማድረግ መንግስት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሙያ ማህበሩ መጠናከር የመምህራንን ጥያቄ በተደራጀ መልኩ ለመመለስና የሃገሪቱን ልማት ለማዘመን እየተካሔደ ባለው ጥረት ውስጥ ጥራት ያለውን የትምህርት ስርዓት ለመገንባት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን መንግስት በፅኑ እንደሚያምን ገልፀዋል ።
ማህበሩ ነጻ በሆነ መልኩ የመምህራንን ድምጽ የሚያሰማ፤ ሃሳብ በማቅረብና አቅጣጫ በማሳየት መንግስትንና ሃገርን የሚደግፍ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን መንግስት ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ የሆነ የትምህርት ሥርዓት ለመዘርጋት የተጀመረውን አጠቃላይ የትምህርት ሪፎርም ሥራ ውጤታማ ለማድረግ የማህበሩ መጠናከር አንዱ አካል በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የመማር ማስተማር ሥራ ለማስጀመር የሚደረገውን ጥረትም በየደረጃው የሚገኙ የመምህራን ማህበር አባላት በማስተባበር የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስትርም የመምህራን የመኖሪያ ቤት፣ የስራ ላይ ስልጠናና መሰል ጥቅማ ጥቅሞች በተገቢው መንገድ እንዲሟሉ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ገልፀዋል ።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው ማህበሩ ባለፉት 70 ዓመታት በተለያዩ ውጣ ወረዶች ቢያልፍም በሃገሪቱ ልማት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን ተናግረዋል ።
ከቅድመ መደበኛ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ከ600 ሺህ በላይ አባላት ያቀፈው ማህበሩ ባበረከተው አስተዋጽኦና በፈጠረው ጠንካራ ግንኙነት ከሃገር አልፎ የዓለም የመምህራን ማህበር ቦርድ አባል ሆኖ ለማገልገል መብቃቱን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ የሚካሄደው 33ኛው መደበኛ ጉባኤ በወቅታዊ ሃገራዊና ትምርታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ገልጸዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት በሃገሪቱ ከተጀመረ አንስቶ የተከሰቱ የመንግስት ስርዓት ለውጦች በስነ-ምግባርና በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ በተፈለገው ልክ ውጤታማ እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡
ይህም መረጋጋት ማጣት ብቻ ሳይሆን ሃገር በቀል ዕውቀቶችን መነሻ ያላደረገ በውጭ አገራት ዕውቀት ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑ ችግሩን አግዝፎታል ነው ያሉት።
አሁን ላይ እየተካሄደ ያለው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሥር ነቀል ለውጥ እንዲያመጣና ከትምህርት ዘርፍ የሚጠበቀውን ውጤት ለማግኘት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ መምህራን የሚጫወቱት ሚና የላቀ መሆኑን ነው አቶ ደስታ ያስረዱት።
መምህራን በተደራጀ መልኩ ማህበራቸው ጠንካራ እንዲሆንና የመምህራን የመኖሪያ ቤትና መሰል ጥያቄዎችን ለመመለስ የክልሉ መንግስት የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ እንደሚጥርም አረጋግጠዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በሚያካሂደው በዚሁ ጉባኤ ያለፈውን ዓመት የስራ ሪፖርት በማድመጥ የ2013 ዓም ዕቅድ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡