ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ ግል ይዞታ የማዛወር ሂደት ለጊዜው መቆሙን የገንዘብ ሚኒስትሩ ገለጹ

ጥቅምት 3/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ግል ይዞታ የማዛወር ሂደት ለጊዜው መቆሙን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ገለጹ።

የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠው የድጎማ በጀት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለክልሉ ካቢኔ እንደማይሰጥም ተገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስቴር በ2013 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል የማዞር ሂደት እየተከናወነ ነው።

በዚህም ኢትዮ-ቴሌኮምን በከፊል ወደግል ይዞታ ለማዛወር የሀብትና የንብረት ግምት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በቅርቡም ጨረታ ወጥቶ በሶስት ወራት ውስጥ ወደ ግል የይዞታ እንዲዛወር ይደረጋል ብለዋል ሚኒስትሩ።

ነገር ግን በአገራዊ ኢኮኖሚ ለውጡ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዛወር የታሰበው እሳቢ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ የዓለምን ኢኮኖሚ ባሽመደመደበት ወቅት አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆኖ መዝለቁን ጠቁመዋል።

በመንግሥት ከሚተዳደሩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የልማት ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀዳሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም አሁን ባለው ሁኔታ አየር መንገዱን ወደ ግል ይዞታ የማዛወር እሳቤ ለጊዜው እንዲቆይ ተደርጓል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚያደርገው የድጎማ በጀት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ያቋርጣል ብለዋል።

ነገር ግን በጀቱ ለክልሉ ካቢኔ ባይሰጥም፤ በክልሉ ወረዳዎችና ከተሞች የሚሰጠው አገልግሎት አይቋረጥም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም