በብር ቅያሪው ሒደት ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በብር ቅያሪው ሒደት ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ተሰጠ
ሁመራ ጥቅምት 03/2013 (ኢዜአ) ከአጎራባች ሀገራት ጋር የሚዋሰነው የትግራይ ምእራባዊ ዞን ህብረተሰቡ የአዲሱ የብር ኖት ቅያሪን ተከትሎ ከሚፈጠረው የማጭበርበር ድርጊት ራሱን እንዲጠብቅ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሳሰበ።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሁመራ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ልጃለም አረፋይነ ለኢዜአ እንዳሉት የብር ኖት ቅያሪን ተከትሎ የሚፈጠሩ የማጭበርበር ተግባራት በአንድ አካል ቁጥጥር ብቻ መከላከል አይቻልም።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ከዞንና ከወረዳ አመራሮችና ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ህገ ወጥ ድርጊትን እንዲከላከል አሳስበዋል ።
ህብረተሰቡ አዲሱን የብር ኖት ለመቀየር የሚያደርገው እንቅስቃሴ በከተሞች የተሻለ መሆኑን የገለፁት ስራ አስኪያጁ በገጠር አካባቢዎች ግን መዘናጋት እንደሚታይ ጠቁመዋል ።
በመሆኑም ህብረተሰቡ የተሰጠውን የማስቀየሪያ ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም አዲሱን የብር ኖት መያዝ እንዳለበት ስራ አስኪያጁ አሳስበዋል ።
በሁመራ ከተማ ልዩ ስሙ ገበያ ማእከል በመባል በሚጠራው ስፍራ በንግድ ስራ የሚንቀሳቀሱ አቶ ሃይለስላሴ ንርአዮ እንዳሉት መጀመርያ አካባቢ አዲሱ የብር ኖት በስነስርዓት ለመለየት ይከብዳቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
ቀስ በቀስ ግን በቀላሉ መለየት እንደቻሉና ከሚደርስባቸው የማጭበርበር ድርጊት ራሳቸውን በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በዞኑ የሚገኙ አንዳንድ አረጋውያንና የገጠር ነዋሪዎች ነባሩን የ100 ብር ከአዲሱ 10 የብር ኖት ጋር እንዲሁም አዲሱን የ’’100 ብር ከነባሩ 5 ብር’’ ጋር የመመሳሰል ባህሪ ስላላቸው ለመለየት ሲቸገሩ መመልከታቸውን የተናገሩት ደግሞ የዶሮ ነጋዴ የሆኑት አቶ ጎይቶኦም አርአያ ናቸው።