የጤና ባለሙያዎች የብቃት ምዘና ከጥቅምት 9 ጀምሮ ለ5 ቀናት ይሰጣል - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ባለሙያዎች የብቃት ምዘና ከጥቅምት 9 ጀምሮ ለ5 ቀናት ይሰጣል
አዲስ አበባ ጥቅምት 3/2013 (ኢዜአ) የጤና ባለሙያዎች የብቃት ምዘና ከመጪው ጥቅምት 9 እስከ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰጥ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የብቃት ምዘና ፈተናውን ከሁሉም የመንግሥትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመጀመሪያ ዲግሪ ለሚመረቁ የጤና ባለሙያዎች ሲሰጥ ቆይቷል።
ይህ ምዘና በሕክምና፣ በነርሲንግ፣ በፋርማሲ፣ በጤና መኮንን፣ በአንስቴዥያ፣ በሕክምና ላቦራቶሪ ቴክኖሎጂና በአዋላጅነት ዘርፍ ለተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጥ ነው።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ሊሰጥ የነበረው ምዘና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሟል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ዓለምፀሃይ ጳውሎስ የተራዘመው የብቃት ምዘና ፈተናው በመላ አገሪቷ በተመረጡ 20 ጣቢያዎች እንደሚሰጥና ለዚህም ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ለሰባቱ የሙያ ዘርፎች 5 ሺህ 991 ሰዎች ምዘና ለመውሰድ መመዝገባቸውን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ ባለሙያዎቹ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ኮቪድ-19ን መከላከልን ከግምት በማስገባትና ጥንቃቄ በማድረግ ፈተናውን እንዲወስዱም አሳስበዋል።
ሚኒስቴሩ ከመጪው ሰኔ 2013 ዓ.ም ጀምሮ የጥርስ ሕክምናና የራዲዮሎጂ የሙያ ዘርፎችን በምዘናው ለማካተት ማቀዱንም ገልጸዋል።
ምዘናው ተግባር ተኮር በሆነ መልኩ በጽሁፍ የሚዘጋጅ ሲሆን በሂደት ወደ ተግባር ፈተና እንደሚሸጋገር ጠቁመዋል።
በተጠቀሱት መስኮች ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ 20 ሺህ 142 ባለሙያዎች የሙያ ብቃት ምዘና የወሰዱ ሲሆን 12 ሺህ 365ቱ ወይንም 61 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆኑት ምዘናውን አልፈዋል።
ፈተናውን ያለፉ ባለሙያዎች የሙያ ሥራ ፈቃድ አግኝተው ለኅብረተሰቡ የጤና አገልግሎት እንዲሰጡ የሚደረግ ሲሆን ፈተናውን ማለፍ ያልቻሉት ደግሞ ምዘናውን ዳግም እንዲወስዱ ይደረጋል።