ተመሳስሎ የተሰራ ሀሰተኛ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ ተገኝተዋል የተባሉ ስምንት ግለሰቦች ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
ተመሳስሎ የተሰራ ሀሰተኛ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ ተገኝተዋል የተባሉ ስምንት ግለሰቦች ተያዙ
ሚዛን፣ ጥቅምት 3/2013 (ኢዜአ) በቤንች ሸኮ ዞን ከ16 ሺህ በላይ ተመሳስሎ የተሰራ ሀሰተኛ የብር ኖት ሲያዘዋውሩ ተገኝተዋል የተባሉ ስምንት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
በቤንች ሸኮ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል ኢንተለጀንስ የስራ ሂደት አስተባባሪ ኢንስፔክተር ስንታየሁ ተገኝ ለኢዜአ እንደገለፁት ግለሰቦቹ የተያዙት ባለፈው ሳምንት በተለያዩ ቀናት ሀሰተኛ የብር ኖቱን ይዘው ግብይት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱና በባንክ ለመቀየር ሲሞክሩ ነው።
በግለሰቦቹ እጅ የተያዘው ከአዲሱ ባለ 200 ብር ጋር ተመሳስሎ የተሰራ 3 ሺህ ሀሰተኛ ኖትና ከነባሩ ባለ 100 ብር ጋር ተመሳስሎ የተሰራ 13 ሺህ 100 ሀሰተኛ ኖት መሆኑን ኢንስፔክተሩ ገልፀዋል ።
ግለሰቦቹ ሊያዙ የቻሉት በባንክ ባለሙያዎችና ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ መሰል ድርጊትን በማጋለጥ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ላይ የምርመራና የማጣራት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ኢንስፔክተር ስንታየሁ ጠቁመው፤ ሂደቱ እንደተጠናቀቀም ለፍርድ እንደሚቀርቡ ገልፀዋል።