ሠንደቅ ዓላማ አንድነታችንን የምናጠናክርበት በመሆኑ በጋራ ልናከብረው ይገባል- የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
ሠንደቅ ዓላማ አንድነታችንን የምናጠናክርበት በመሆኑ በጋራ ልናከብረው ይገባል- የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ
ሀዋሳ/ድሬዳዋ / ጥቅምት 2/2013 (ኢዜአ ) ሠንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች የሉአላዊነት መገለጫና አንድነት የሚጠናከርበት በመሆኑ በጋራ ሊከበር እንደሚገባ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ሰለሞን ላሌ አሳሰቡ።
የሠንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በሲዳማ ክልልና በድሬዳዋ አስተዳደር ተከብሯል።
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ሰለሞን ላሌ በበዓሉ ስነ-ስርዓት እንዳሉት ሠንደቅ ዓላማን ከመስቀል ባለፈ ተገቢውን ክብር መስጠት ይገባል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች የሉአላዊነት መገለጫ የሆነውን ሠንደቅ ዓላማ አንድነታችንን የምናጠናክርበትና የጋራ መግባቢያችን በመሆኑ በጋራ ልናከብረው ይገባል ብለዋል።
አቶ ሰለሞን ሠንደቅ ዓላማውን ለማክበር በጋራ እንደተወጣው ሁሉ ብሔሮች ብሔረሰቦች አንድ ላይ በመሆን ኢትዮጵያን ማልማት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው የማንነታችን መገለጫ የሆነው የሠንደቅ ዓላማ ክብርና ስርዓት በተገቢው መንገድ በመፈጸም ወጣቱ ትውልድ የዘወትር ተግባሩ እንዲያደርገው ማስተማር ይገባል ብለዋል።
በቀደምት አባቶች የነበረው የሠንደቅ ዓላማ ክብር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተቀዛቅዞ እንደቆየ አውስተው ይህን ለመመለስ በተለያዩ ዝግጅቶች የሠንደቅ ዓላማን ክብር ለወጣቱ ትውልድ ማስረጽ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ጀግኖች አባቶቻችን የደም መስዋዕትነት ከፍለው ለዛሬ ያደረሷትን ሀገር እኛም ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረታችንን ሀገር በማልማት ላይ ማድረግ አለብን ብለዋል።
በተመሳሳይ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በድሬዳዋ ሲከበር የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋ እንደተናገሩት፤ በተለይ ወጣቶች በሀገሪቱም ሆነ በድሬዳዋ የሚስተዋለውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ በማድረግ የተጀመረው የልማት ጉዞ ውጤታማ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።
ወጣቶች የሥራ ዕድል በማመቻቸት በሀገር ግንባታና ልማት ላይ የማይተካ ሚና እንዲጫወቱ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ከቤተሰብ ጀምሮ በትምህርት ቤቶች ወጣቶች ለሠንደቅ ዓላማና ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር እንዲያጎለብቱ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ተፈሪ መሠረት በሰጡት አስተያየት የሠንደቅ ዓላማ ክብርን በአዲሱ ትውልድ ውስጥ ማስረፅና የኔነትን መንፈስ ማጎናፀፍ ለሀገር ግንባታና ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የበዓሉ ተሳታፊዎች በየተሰማሩበት የሥራ መስክ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት ሀገሪቱ ከድህነት ለመውጣትና ወደ ብልጽግና እንድትጓዝ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በጋራ ቃል ገብተዋል።
በሲዳማና ድሬዳዋ በዓሉ ሲከበር የሠንደቅ ዓላማ የመስቀል ስነ-ስርዓትም ተካሄዷል።