ቀጥታ፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለለውጥ ፈላጊ ወገን ወሳኝ ነው -ትዴፓ

ጥቅምት አዲስ አበባ 2/2013 (ኢዜአ)የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለለውጥ ፈላጊ ወገን ወሳኝ ነው ሲል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ገለጸ። 

ትዴፓ በትግራይ ክልል እየተካሄዱ ያሉ እንቅስቃሴዎችንና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን አስመልክቶ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

በዚህም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቅርቡ ያሳለፈው ውሳኔ ለትግራይ ህዝብም ሆነ አገራዊ ለውጡን ለሚፈልግ ወገን ወሳኝ ነው ሲል ገልጿል።

 ለውሳኔው ተግባራዊነት የሚመለከታቸው አካላት መስራት እንደሚኖርባቸውም ሀሳብ አቅርቧል።

   በትግራይ ክልል ሁሉንም ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ ዴሞክራሲያዊ እና ነፃ ምርጫ ለማካሄድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ህገ-መንግስታዊ ግዴታውን እንዲወጣም ፓርቲው በአቋም መግለጫው አመልክቷል።

    በትግራይ ክልል ያለው ''ልዩ ኃይል'' አንድም በፌዴራል ሠራዊት ማዕቀፍ ሥር፣ አልያም በፌዴራል ፖሊስ እዝ ሥር ተጠቃሎ ህገ-መንግስታዊ ግዳጁን ሊፈጽም ይገባዋል ሲልም ሀሳብ አቅርቧል።

    ህወሓትና አጃቢ ፓርቲዎቹ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ውጪ ህገ-ወጥ ምርጫ በማካሄዳቸው ከምርጫ ቦርድ የተሰጣቸው ዕውቅና እንዲሰረዝም ፓርቲው በአቋም መግለጫው ጠይቋል።

    በትግራይ ክልል ላይ በፌዴራል መንግስትም ሆነ በሌሎች መንግስታዊ አካላት የሚወሰዱ እርምጃዎች ህገ-መንግስቱን የተከተሉና የትግራይን ህዝብ ጥቅሞችና ሠላማዊ ኑሮ በማይጎዳ መልኩ መተግበር እንዳለባቸውም ትዴፓ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም