ቀጥታ፡

ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆነ

አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2010 ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የ2010  የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆኗል። የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንትና ዛሬ ተካሂደዋል። ዛሬ በድሬዳዋ በተካሄደ ጨዋታ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 22 ለ 18 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዘንድሮ የሊጉ አሸናፊ መሆን ችሏል። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ባደረጋቸው 16 ጨዋታዎች 28 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። መቐለ ከተማ በሜዳው ከምባታ ዱራሜን 30 ለ 27 በማሸነፍ በአጠቃላይ 23 ነጠብ ሁለተኛ ደረጃ ይዟል። ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ መከላከያ ፌዴራል ፖሊስን 32 ለ 22 በማሸነፍ በ22 ነጥብ ሶስተኛ ወጥቷል። ቡታጅራ ላይ ፌዴራል ማረሚያ ቡታጅራ ከተማን 28 ለ 22 በሆነ ውጤት ረትቷል። ዘጠኝ ቡድኖች በተሳተፉበት የሊጉ ውድድር ቡታጅራ ከተማ ሁለት ነጥብ ብቻ አግኝቶ የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ መቐለ ከተማና መከላከያ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመያዝ የሜዳሊያ ሽልማት ያገኙ ሲሆን ሻምፒዮኑ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከሜዳሊያው በተጨማሪ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል። መቐለ ከተማ የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። የቂርቆስ ክፍለ ከተማው ተጫዋች እንዳለ አበበና የቂርቆስ ከተማው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ግርማ በቅደም ተከተል የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋችና አሰልጣኝ በመሆን ተመርጠዋል። በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚካሄደው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ባለፈው ዓመት ሲጀመር መከላከያ የመጀመሪያው አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም