ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚደረጉ ለውጦች የሕግ የበላይነትን መሰረት እንዲያደርጉ ተጠየቀ

 አዲስ አበባ፤ ጥቅምት  2/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ለውጦች በሙሉ የሕግ የበላይነትን መሰረት እንዲያደርጉ ባለሙያዎች ጠየቁ። 

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሕግ የበላይነትና በፍትህ አካላት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን አስመልክቶ ጥናት እያደረገ ይገኛል።

ጥናቱ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ሲሆን፣ ዛሬ ከሕግ ባለሙያዎችንና ከፍትህ አካላት ጋር በመወያየት ለጥናቱ ግብዓቶች ሰብስቧል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የሕግ ባለሙያዎች አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የፍትህ አካላትን አደረጃጀት ለማሻሻል እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የሕግ ጥሰቶች መፈጸማቸውን አመልክተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ ለውጦች በሙሉ የሕግ የበላይነትን መሰረት ሊያደርጉ እንደሚገባቸው ነው በሕግ ባለሙያዎቹ የተነሳው።

በተለይ በፍርድ ቤቶች አካባቢ የአስፈጻሚው ጣልቃ ገብነት እየጎላ መምጣቱ የፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዳይከበሩ ማድረጉና  ሙስናና ብልሹ አሰራሮች መባባሳቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች በህዝብና በመንግስት መካከል መተማመን እንዳይኖር አድርጓል ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ በርካታ ለውጦች እየታዩ ቢሆንም ህግና ስርዓትን በማክበርና በማስከበር በኩል ጉልህ ከፍተቶች መታየታቸውን አልሸሸጉም።

የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ፤ ሁሉም አካላት ድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተገልጿል።

የኢንስቲትዩቱ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ያሲን መሐመድ በበኩላቸው ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ሕግ የማውጣት ሂደት ቢኖርም፤ አተገባበሩ ላይ ግን ክፍተት መኖሩን አንስተዋል።

ማዕከሉ የችግሩን አንገብጋቢነት በመረዳት ለሚመለከታቸው አካላት የመፍትሄ ሀሳብ ለመስጠት ጥናት ማካሄዱንም ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በሕግ የበላይነትና በፍትህ አካላት ላይ እያካሄደ ያለው ጥናት የተለያዩ ግብዓቶች ታክለውበት በህዳር ወር ይፋ እንደሚሆንም ዶክተር ያሲን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም