ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከተሞችን መልካም ገጽታ ለመገንባት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ስራ ያስፈልጋል

ባህርዳር፣ ጥቅምት 2/2013( ኢዜአ) የኢትዮጵያን ከተሞች ፅዱ፣ ወብና አረንጓዴ በማድረግ መልካም ገፅታቸውን ለመገንባት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ስራ እንደሚያስፈልግ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ገለጸ።

"ንፁህናና  አረንጓዴ ከተሞች ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ የዓለም ከተሞች ቀን በሃገር ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በባህርዳር እየተከበረ ይገኛል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መስፍን አሰፋ በዓሉን አስመልክቶ በተካሄደው ጉብኝት ወቅት እንደተናገሩት የሀገሪቱን ከተሞች ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ ነው።

ከቆሻሻ የፀዱ፣ ሳቢ፣ ውብና አረንጓዴ ከተሞችን ለመፍጠር  እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ የከተማ አስተዳደሮች፣ ህብረተሰቡን፣ ባለሃብቱንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ስራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ከተሞች ብዙ ህዝብ በአንድ ላይ ተጠጋግቶ የሚኖርባቸው ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ዘመናዊ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ትኩረት በመስጠት የነዋሪዎችን ጤንነትና ደህንነት መጠበቅ ይገባል ብለዋል።

የከተማ ነዋሪውን አስተሳሰብና አመለካከት በመለወጥም ጨለማን ተገን አድርጎ ቆሻሻን በመጣልና የሚጸዳዱ ግለሰቦችን በመቆጣጠር አካባቢን ከብክለት ነጻ ለማድረግ ተከታታይነት ስራ ይጠይቃል።

ይህም ለኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምን መስፋፋትና ነዋሪዎች ምቹ ከተማ ለመፍጠር የተያዘውን ግብ ለማሳካት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ የከተሞች ሚና መሆን አለበት ብለዋል።  

የባህርዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ በበኩላቸው የባህርዳር የጣናና አባይ ወንዝ መገኛ በመሆኗ ለነዋሪዋቿና ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች የተመቸች ከተማ ናት ብለዋል።

ይህን ምቹ ሁኔታ በመጠቀምም የከተማ አስተዳደሩ አከባቢውን በአረንጓዴ ልማት ለመሸፈን የሚያግዙ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

የከተማዋን ዘላቂ ጽዳትና ውበት ለማስጠበቅም በጥቃቅንና አነስተኛ በተደራጁ ማህበራት አማካኝነት የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ተዘርግቶ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት በተካሄደው የህግ ማስከበር ስራ ከ38ሺህ 400 በላይ ህገ ወጥ ግንባታዎችን በማፍረስ የሰላምና የኢንዱስትሪ ከተማ ለማድረግ የተሰራው ስራ ውጤታማ ነበር ብለዋል።

በዚህም ከ450 የሚበልጡ ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ወደ ከተማዋ መምጣታቸውን ጠቁመው እነዚህንና ሌሎች ባለሃበቶችን ለማስተናገድ የሚያስችል 500 ሄክታር መሬት  መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ባህርዳርን  የቱሪዝምና ኢንዱስትሪ ከተማ ለማድረግ በሚካሄደው እንቅስቃሴ ሚንስቴሩ  በቅርበት እንዲደግፍም ጠይቀዋል።

ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የመጡት ወይዘሮ ዝናሽ ሙሉ በሰጡት አስተያየት የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ውጤት እንዳመጣ መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

ተዘዋውረው የጎበኟቸው ሰፋፊ የህዝብና የማህበረሰብ የአረንጓዴ ልማት ፓርኮችም ለሌሎች ከተሞች ልምድና መልካም ተሞክሮ  እንደሚሆንም ጠቅሰዋል።

የአረንጓዴ ቦታዎችን ከማልማት  ባሻገር በአግባቡ መጠበቅ፣ በውስጣቸው የህፃናት መጫዎቻዎችና መቀመጫ ቦታዎች በበቂ ሁኔታ ቢኖሩ ይበልጥ ሳቢ ማድረግ እንደሚቻል አስተያየት ሰጥዋል።

የዓለም የከተሞ ቀን በዓለም ለሰባተኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ በባህርዳር ከተማ በጉብኝት የተጀመረው ስነ-ስርዓት ነገም በፓናል ውይይት እንደሚቀጥል ታውቋል።

በበዓሉ  ከአማራና ከሌሎች ክልሎች ዋና ዋና  ከተሞች እንዲሁም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም