የኅብረተሰቡን የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሳደግ አማራጮችን ማስፋት ይገባል - ብሔራዊ ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
የኅብረተሰቡን የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሳደግ አማራጮችን ማስፋት ይገባል - ብሔራዊ ባንክ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2/2013(ኢዜአ) ኅብረተሰቡ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን የተለያዩ አማራጮችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ተናገሩ፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጠው ዘምዘም ባንክ የስራ ፈቃዱን ተረክቧል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ኅብረተሰቡን የዘመናዊ ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ እተከፈቱ ያሉ መደበኛና ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎቶች ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጠው ዘምዘም ባንክ በተለይ የገጠሩ አካባቢ ኅብረተሰብ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ቅርንጫፎቹን በማስፋት ተደራሽነቱን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
ባንኮችን ዘመናዊና ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ሪፎርሞች እየተተገበሩ ነው ያሉት ዶክተር ይናገር ዘምዘም ባንክ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ባንክ የማምጣት ሚናው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘምዘም ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ናስር ዲኖ ባንኩ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ፊርማና ከ875 ሚሊዮን ብር በላይ ተከፋይ ይዞ ለምስረታ መብቃቱን ገልጸዋል።
የባንኩ ዋና ስራአስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ወይዘሮ መሊካ በድሪን በበኩላቸው ባንኩ ተወዳዳሪ ሳይሆን አማራጭ ይዞ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል።