ቀጥታ፡

ቤተክርስቲያኗ ሕዝቡ የአንበጣ መንጋ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ድጋፍ እንዲያደርግ ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከባድ በመሆኑ ሕብረተሰቡ የሚችለውን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጠየቀች።

ቤተክርስቲያኗ ለኢዜአ በላከችው መግለጫ አርሶ አደሩ በባሕላዊ መንገድ፤ መንግስትም ባለው አቅም ሁሉ አንበጣውን ለመከላከል እያደረጉት ያለውን ጥረት መላው ሕዝብ በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ እንዲያግዝ ጥሪ አስተላልፋለች።

ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም የአንበጣ መንጋውን ለማጥፋት የመድሃኒት፣ የባለሙያና የመድሃኒት መርጫ አውሮፕላን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቃለች።

አርሶ አደሩ የመጨረሻ መከሩን ለመሰብሰብ በሚጠብቅበት ወቅት ያልታሰበው የአንበጣ መንጋ የደረሰውን ሰብል ሲያጠፋው ማየት "ልብ የሚሰብር ክስተት ነው" ይላል መግለጫው።

መጪው ጊዜ ምርቱ የወደመበትን አርሶ አደር ለረሃብና ለችግር፣ ምርቱን ለሚጠብቀው ሕዝብ ደግሞ ተጨማሪ የኑሮ መዛባት የሚያመጣ መሆኑንም ጠቅሷል።

ክስተቱ "ለአገራችንና ለወገናችን በፍቅር፣ በመተሳሰብና በመወያየት መፍትሄ እንድናመጣ አመላካች ነው" ስትል ቤተክርስቲያኗ አመላክታለች።

በመሆኑም የአብዛኛው የአገሪቷ ሕዝብ መተዳደሪያ በሆነው በግብርና ምርት ላይ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ምርቱንና የአርሶ አደሩንም ስነ ልቦና በሚጎዳ መልኩ በመከሰቱ "ሁላችንም ለወገኖቻችን ድጋፍ ለመስጠት በአንድ ልብ ሆነን ልንነሳ ይገባናል" በማለት አሳስባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም