ቀጥታ፡

በሩብ ዓመቱ ከማዕድን ዘርፍ ከ178 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2/2013(ኢዜአ) የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በ2013 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከማዕድን ዘርፍ ከ178 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ2013 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫውም የውጭ ምንዛሬ የተገኘው ወርቅ፣ ታንታለም፣ ኳርትዝ፣ ኢመራልድ፣ ሳፓየር እና እምነ-በረድ የተሰኙ ማዕድናት ወደ ውጭ በመላክ ነው።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንደገለጹት በሩብ ዓመቱ ከማዕድን ዘርፉ ከ178 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡

በቀጣይ ጊዜያት የተጀመሩ የመሪ ዕቅድ ዝግጅቶች፣ የፖሊሲ ማስተካከያዎች፣ የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያ የሰነድ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ እና ተቋማዊ ግንባታውን አጠናክሮ በማስቀጠል ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

"የተቋሙ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ዝግጅት ተጠናቆ ለሚመለከታቸው አካላት ተልኳል" ያሉት ኢንጂነር ታከል፣ የወርቅ ቤተ-ሙከራ ለማቋቋም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሰነድ ዝግጅቶቹ ከዘርፉ ህብረተሰቡን በፍትሐዊነት ተጠቃሚ በማድረግ አገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማገዝ የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተቋሙ የተዘጋጀው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ግቡን እንዲመታም ከክልል መንግስታት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

እንደሚኒስትሩ ገለጻ የማዕድንና ነዳጅ ዘርፉን የፍለጋና የምርት ሂደት ምቹና ሰላማዊ ለማድረግ ከክልል መንግስታት ጋር በትኩረት እተሰራ ነው፡፡

በሩብ ዓመቱ 750 ኪሎ ግራም ወርቅ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ 2 ሺህ 241 ኪሎ ግራም ወርቅ ለገበያ ማቅረብ እንደተቻለና ይህም የዕቅዱ 298 ነጥብ 9 በመቶ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዕቅድ በላይ ለተገኘው ውጤትም ብሔራዊ ባንክ ያደረገው የወርቅ ግብይት ማሻሻያ አቅራቢዎችን በመሳቡ በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያቀርቡትን ጭምር መሳብ በመቻሉ እንደሆነም አቶ ታከለ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት የማዕድን ምርት ሂደቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩንም ነው የገለጹት

በመግለጫው ከማዕድንና ነዳጅ ዘርፉ ህብረተሰቡ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲጠቅም ዘርፉ በእቅድ የሚመራ እና ጠንካራ የሰው ኃይል አደረጃጀት እንዲኖረው የሚደረግ መሆኑን ተገልጿል።

"ዘርፉ ለአገር በቀል ኢኮኖሚው ማቀላጠፊያ እንዲሆንም በትኩረት ይሰራል" ብለዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ በዘመናዊ መንገድ፣ በጥናትና በአግባቡ ተመርቶ ጥቅም ላይ ከዋለ የአገርን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል የአገር ሀብት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም