ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ኤርፖርት 1 ነጥብ 4 ኪሎግራም ወርቅ ሊወጣ ሲል ተያዘ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ኤርፖርት በአንድ የውጭ ዜጋ ከአገር ሊወጣ የነበረ 1 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም ወርቅ በቁጥጥር መዋሉን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለኢዜአ እንደገለጸው ወርቁ ከአገር ሊወጣ ሲል የተያዘው ለዲፕሎማቶች ዕቃ የሚሰጠው ያለመፈተሽ መብት ያለው አስመስሎ ለማሳለፍ ሲሞክር ነው።

ግለሰቡ ራሱን በካሜሩን ኤምባሲ የሚሰራ ዲፕሎማት አስመስሎ ወርቁን በታሸገ ፖስታ አድርጎ ለማለፍ መሞከሩንም አስረድቷል።

ከዚህም በላይ ግለሰቡ ፖስታውን እንዲያስፈትሽ ሲጠየቅ ፈቃደኛ እንዳልነበርም ኮሚሽኑ አመልክቷል።

ኮሚሽኑ የግለሰቡን ማንነት በውጭ ጉዳይ  ሚኒስቴር በኩል በተደረገው ማጣራት የአገሪቱ ኤምባሲ  ''ግለሰቡንም ሆነ በፖስታው ውስጥ ያለው እሽግ''እንደማያውቅ በደብዳቤ አረጋግጧል ብሏል።

ከግለሰቡ የተያዘው ወርቅ  መረጃው እስኪጣታ ለ13 ቀናት በኤርፖርቱ መቆየቱን ገልጿል።

ወርቁ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ  ገቢ መደረጉን ኮሚሽኑ በመግለጫው አመልክቷል።ግምታዊ ዋጋውም 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር መሆኑንም አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ወርቁ ለያዙት የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትና የአቪዬሽን የደህንነት ሰራተኞች ምስጋናውን አቅርቧል።

ኮሚሽኑ ባለፈው ወር  የዚምባብዌ  ዜግነት ባለው መንገደኛ ገንዘብ ይዞ መግባቱን ይፋ ሳያደርግ 132 ሺህ 860 ዶላር ይዞ ከአገር ለማውጣት ሲሞክር ይዟል።

ገንዘቡንም ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ኮሚሽኑ አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም