የሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነት የሥርዓተ-ምግብ ተጠቀሚነትን አሻሽሏል --- ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነት የሥርዓተ-ምግብ ተጠቀሚነትን አሻሽሏል --- ተጠቃሚዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነት ተጠቃሚ እናቶች የሥርዓተ-ምግብ ተጠቃሚነታቸው መሻሻል ማሳየቱን ተናገሩ።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት በተከዜ ተፋሰስ አከባቢ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚስተዋልባቸውን የመቀንጨር ችግር በ2022 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ማጥፋትን ግብ ያደረገ ነው።
በዚህም ነፍሰ-ጡር እና ወላድ እናቶች እንዲሁም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት የሥርዓተ-ምግብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት ተደርጓል።
በተለይም አቅም የሌላቸው እናቶች ከሚፈጠርላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ በተጨማሪ ዶሮ፣ ፍየል፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በነጻ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።
በአንጻሩ አቅም ያላቸው እናቶች በግብርና ጣቢያዎች የሚዘጋጁ የጓሮ አትክልትና የፍራፍሬ ዘሮችን እንዲያገኙ ይደረጋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎች ስምምነቱ የሥርዓተ-ምግብ ተጠቃሚነታቸውን እያሻሻለው መምጣቱን ነው የገለጹት።
ይህም ሆኖ ነዋሪዎቹ በብዛት ከሚያገኙት የዶሮና የእንቁላል ድጋፍ በዘለለ የአትክልትና ፍራፍሬ አቅርቦት ላይ እጥረት መኖሩን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የንጹህ ውሃ ተጠቃሚነት በፊት ከነበረው መሻሻሉን የተናገሩት የሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎች፣ ከዚህ ቀደም ውሃ ለማግኘት የነበረባቸው ችግር በአሁኑ ወቅት በተወሰነ ደረ መቃለሉን ጠቁመዋል።
አካባቢው ውሃ አጠር በመሆኑ ችግሩ አሁንም ሙሉ በሙሉ አለመቀረፉንና አሁንም እናቶች ከምንጭ ውሃ እየተጠቀሙ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት ሥራአስኪያጅ አቶ ተፈራ ቢራራ "ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ይዘን አየሰራን ቢሆንም ችግሮች አሉ" ብለዋል።
በተለይም አካባቢው ውሃ አጥር በመሆኑ የአትክልትና ፈራፍሬ ሥራዎችን ለመስራት የሚያስፈልገውን ውሃ ለማግኘት አዳጋች በመሆኑ የእንስሳት ተዋጽጾ ላይ ትክረት መደረጉን ነው ያስረዱት።
ያም ሆኖ በተለይ በደጋ አካባቢዎች ላይ በሚገኘው የዝናብ ውሃ እናቶች የጓሮ አትክልት በቋሚነት አልምተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሰራቱን አስረድተዋል።
በአካባቢው የውሃ አቅርቦቱን ለማስተካከል እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ ሃብት ማሰባሰብና አዲስ መርሃ ግበር መቀየስ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት በአማራ ክልል በአምስት ዞኖች ውስጥ ባሉ 27 ወረዳዎች የሚኖሩ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል።