የሰንደቅ ዓላማ እሴቶችን በየደረጃው ማስተማር ያስፈልጋል ---የምክርቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የሰንደቅ ዓላማ እሴቶችን በየደረጃው ማስተማር ያስፈልጋል ---የምክርቤት አባላት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እሴቶች ለትውልድ በማስተማር ለአገር እድገት እንዲተባበር ማድረግ ይገባል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ተናገሩ።
13ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ዛሬ ተከብሯል።
የምክርቤት አባላት ለኢዜአ እንዳሉት ሰንደቅ ዓላማ የአንድነት፣ እኩልነት፣ ወንድማማችነት፣ መተባበርና ኢትዮጵያዊነት ፍቅር የሚንጸባረቅበት ዓርማ ነው።
ወይዘሮ መስከረም አልጋዬ እንዳሉት ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ተስፋና ጀግንነት የሚታይበት ነው።
ኢትዮጵያውያን በመተባበርና በአንድነት ለአገራቸው ነጻነት ታግለው ያቆዩትን አገር በምጣኔ ሃብት እድገት በዓለም ከፍ ብላ እንድትታይ ማድረግ እንደሚገባ በአጽንኦት አንስተዋል።
በመሆኑም ከቤተሰብ ጀምሮ የሰንደቅ ዓላማን እሴቶችን ለትውልድ ማስተማርና ማጎልበት ይገባል ይላሉ።
ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ዘለቀ መሃሪ በበኩላቸው ሰንደቅ ዓላማ ብሔር/ብሔረሰቦች ለአገራቸው አንድነት፣ ሰላም፣ ብልጽግና እንዲሁም ከጭቆና አገዛዝ ነጻ ያወጡበት የትብብር መለያ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላለውና ለመጪው ትውልድ የሰንደቅ ዓላማ ውክልና ለሕዝቦች ነጻነትና ለአገር ሉአላዊነት በመሆኑ ማስተማር ያስፈልጋል ብለዋል።
ሰንደቅ ዓላማ የሁሉም ብሔር /ብሔረሰቦች ተጋድሎ ያደረጉለት መሆኑን ባካተተ መልኩ ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል።
መጪው ትውልድ የሰንደቅ ዓላማውን ክብር በመጠበቅ በአንድነትና በጋራ እንዲተባበር የሚናገሩት ደግሞ አቶ መሐመድ አልሃሊ ናቸው።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተሻሻለው ሰንደቅ ዓላማ ዓዋጅ ቁጥር 863/2006 አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ የጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሰኞ ይከበራል።