ቀጥታ፡

ኀብረተሰቡ የሰንድቅ ዓላማ ክብርን በመጠበቅ የለውጥ ድሎችን ለማስቀጠል በጋራ ሊሰራ ይገባል

ጋምቤላ፣ ጥቅምት 2/13 (ኢዜአ) ኀብረተሰቡ የብሔራዊ ማንነት መገላጫ የሆነውን የሰንድቅ ዓላማ ክብር በመጠበቅ የለውጥ ድሎችን ለማስቀጠል በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስገነዘቡ።

’’ሰንደቅ ዓለማችን ለሰላማችን፣ ለአብሮነታችና ለሀገራዊ ብልጽግናችን’’በሚል መሪ ቃል ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በክልል ደረጃ በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት የህዝቦች የአንድነት መገለጫ የሆነውን የሰንደቅ ዓላማ ክብር  በመጠበቅ የተጀመሩ ሀገራዊ የለውጥ ድሎችን ለማስቀጠል በጋራ መሰራት ይገባል።

የተጠናቀቀው በጀት ዓመት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የኮሮና ወረርሽኝ ተጽዕኖ በመቋቋም ታላላቅ ስኬቶች መመዝገባቸውን አስታውሰዋል።

በዘንሮው በጀት አመት ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ጨምሮ በክልል ብሎም በሀገቱ የታቀዱ የልማት እቅዶችን ስኬታማ ለማድረግ ከህዝቡ በተለይም ከወጣቱ የላቀ ሚና እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ያልተዋጠላቸው ኃይሎች ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም እያሉ ህዝቡን ለማደናገር ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱን ጠቅሰዋል።

ህዝቡ ሀገራዊ ለውጡ ያልተዋጠላቸው ኃይሎችን እኩይ ተግባር መመከት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በስነ ስርአቱ ላይ ከተሳተፉ መካከል የክልሉ ፓሊስ አባል ኮማንደር ዳዊት ደቦል "ሰንደቅ ዓላማ የሀገርና የማንነት መገለጫ አርማ ነው" ብለዋል።

ፖሊስም ሆነ ሌላው የሰራዊት ኃይል ለሰንደቅ ዓላማ የተለየ ፍቅር እንዳለው በመግለጽ ስራዊቱ የሰንደቅ ዓላማን ክብር ለማስጠበቅ ጠንክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

"ሰንደቅ ዓላማ የብሔራዊ ኩራት መገለጫ ስለመሆኑ በወጣቱ ዘንድ የግንዛቤ ክፍተት አለ"ያሉት ደግሞ ሌላው የበዓሉ ታዳሚ አቶ ኃይለማርያም ተክለማርያም ናቸው።

"የወጣቱን ግንዛቤ በማሳደግ ለሰንደቅ ዓላማ የተለየ ክብርና ፍቅር እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ የከተማ ነዋሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም