ኮርፖሬሽኑ ለመተማ ዮሐንስ ከተማ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንፎርመር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ ለመተማ ዮሐንስ ከተማ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንፎርመር ድጋፍ አደረገ
ገንዳ ውሃ፣ ጥቅምት 02/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ መከላከያ ኢንጅነሪንግና ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን በምዕራብ ጎንደር ዞን ለመተማ ዮሃንስ ከተማ ህዝብ አገልግሎት የሚውል 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የኤለክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንፎርመር ድጋፍ አደረገ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሌተናል ኮሎኔል ስለሽ ነገራ በድጋፍ አሰጣጡ ስነ-ስርዓት የመከላከያ ኃይላችን የህዝብን ሰላምና ደህነነት ከማስጠበቅ ባሻገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍታት ተጨማሪ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
አሁን ላይም የመተማ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎችን የመብራት አቅርቦት ችግርን ለማቃለል "ባለ 630 ኪሎ ቮልት "የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንፎርመር ማበርከቱን አስታውቀዋል።
በቀጣይም ኮርፖሬሽኑ ሌሎች የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግሮችን ለማቃለል ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር እንደሚደግፍ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡም የአካባቢውን ዘላቂ ሰላም በማስከበር የልማት ቀጠና ለማድረግ የድርሻውን እንደሚወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀብቴ አዲሱ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ያደረገው የትራንስፎርመር ድጋፍ ለዘመናት የዘለቀውን የህብረተሰቡ ጥያቄ ለመመለስ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ከተቋሙ የተደረገው የትራንስፎርመር ድጋፍ መከላከያ የህዝብ መሆኑን ዳግም ያረጋገጠበት መሆኑን ተናግረዋል።
"ባለፉት ዓመታት አካባቢው እንዳይለማና በህዝቦች መካከል ጥርጣሬ እንዲሰፍን በማድረግ የሰው ህይወትና ንብረት እንዲወድም ከፍተኛ ሴራ ሲሰራ ቆይቷል" ብለዋል።
የመከላከያ ሰራዊቱ ቆራጥ እርምጃ በመውሰዱ የአካባቢው ሰላም ወደ ነበረበት መመለስ መቻሉን ጠቁመው ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ኃይማኖት አባቶችና ከህብረተሰብ ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በርክክቡ ስነ-ስርዓት የአካባቢው ማህበረሰብና የአስተዳደር አካላት እንዲሁም የክልሉና የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡