ቀጥታ፡

ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአልሙኒየም ሽት የሰረቁ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2013 (ኢዜአ) የግለሰብ መጋዘን በመስበር ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአልሙኒየም ሽት የሰረቁ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከ500 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸውን የአልሙኒየም ሽት የሰረቁ ተጠርጣሪዎችን እጅ ከፍንጅ መያዙን ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ በክፍለ ከተማው ወረዳ 10 ልዩ ቦታው "ፋሪስ ሰፈር" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ የግለሰብ መጋዘንን ትናንት ከሌሊቱ 9 ሰዓት አካባቢ ሰብረው በመግባት የስርቆት ወንጀሉን መፈጸማቸውን የእፎይታ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ዮሐንስ ሸንዶ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ወደ መጋዘኑ በመግባት ግምታቸው 533 ሺህ ብር የሆነ 227 ፍሬ የአልሙኒየም ሽት ሰርቀው የሰሌዳ ቁጥሩ 3- 17455 ኦ ሮ  በሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ ጭነው ለመሰወር ሲሞክሩ የአካባቢው ህብረተሰብ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክተዋል።

በዕለቱ የመጋዘኑ የጥበቃ ሠራተኛ የነበረው ግለሰብ ስለሁኔታው ሲጠየቅ "ተኝቼ ነበር" የሚል ምላሽ መስጠቱን ገልጸዋል።

ጥበቃው ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ እሱን ጨምሮ በቁጥጥር ስር በዋሉ አምስት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ምክትል ኢንስፔክተር ዮሐንስ ገልጸዋል።

ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል እና ወንጀል ፈጻሚዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚከናወነው ተግባር ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም