ቀጥታ፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ እግር ኳስ ክለብ ከፕሪሚየር ሊጉ ተሰናበተ

አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2010 የኢትዮ ኤሌክትሪክ እግር ኳስ ክለብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወደ ብሄራዊ ሊግ ወረደ። የኢትዮጵያ ወንዶች ፕሪምየር ሊግ  የመጨረሻ ጨዋታዎች ከአርብ ጀምሮ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በመካሄድ ላይ ናቸው። ትላንት በዝናብ ምክንያት የተቋረጠው የድሬዳዋና  የወልዋሎ ዓዲ ግራት ዩኒቨርስቲ ጨዋታ ዛሬ ረፋዱ ላይ ተካሂዶ በድሬዳዋ 2 ለ ባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል። ይህንን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወልደያና አርባ ምንጭ ከተማን ተከትሎ ሶስተኛው ወራጅ ክለብ ሆኗል። ኢትዮ ኤለሌክትሪክ ምንም አንኳን ትናንት ሲዳማ ቡናን 2 ለአንድ በሆነ ውጤት ማሸነፍ ቢችልም ከመውረድ  አልተረፈም። የመውረድ ስጋት የነበረው ድሬዳዋ ከተማ  ወልዋሎ ዓዲ ግራት ዩኒቨርስቲን ማሸነፉን ተከትሎ በነጥብ  ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር እኩል ቢሆንም በግብ ክፍያ በልጦ በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል። በ1953 ዓ.ም የተመሰረተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፕሪሚየር ሊጉ በአዲስ ከተጀመረበት ጀምሮ ሁለት ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ሆኗል። ነገ የሊጉን አሸናፊ የሚለይበት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ከቀኑ 8፡00  ሰዓት ይደረጋሉ። አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ከጅማ አባጅፋር፤  አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ይጫወታሉ። ቅዱስ ጊዮርጊስና ጅማ አባ ጅፋር በእኩል 52 ነጥብና በእኩል የጎል እዳ ሊጉን እየመሩት ይገኛሉ።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም