ቀጥታ፡

አገራዊ ምርጫው ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሰረት ጥሎ ማለፍ አለበት ---ተፎካካሪ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2/2/2013 (ኢዜአ) ስድስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሰረት ጥሎ እንዲያልፍ በመስራት ላይ መሆናቸውን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የ78 ፖለቲካ ፓርቲዎች ህጋዊነትን እያጣራ መሆኑን አስታውቋል።


ፓርቲዎቹ በምርጫ አሸንፈው መንግሥት መሆን የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት መሰረት ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበት አገራዊ ምርጫ በዓለም አቀፉ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙይታወቃል።


ጤና ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው አካላት ወረርሽኙን ታሳቢ ያደረጉ የመከላከል ሥራዎችን በማከናወን ምርጫውን ማካሄድ እንደሚቻል ምክረ ሀሳብአቅርበዋል።


ምርጫው የሚካሄድበት ቀነ ገደብ ባይቀመጥም፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ።


አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በአገሪቷ ቀደም ሲል በአምስት ዙሮች የተካሄዱትን ምርጫዎችንይተቻሉ።


ነጻ፣ገለልተኛና በሕዝብ ዘንድ አመኔታ የተቸራቸው ምርጫዎች ባለመካሄዳቸው በአገሪቷኢ-ዴሞክራሲያዊ አሰራር ኣለመኖሩን ማሳያ ነው ብለዋል።


 ''ያለፉትን አምስት ምርጫዎች ከደርግና ከንጉሱ ምርጫ ለይቼ አላያቸውም'' ያሉት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) ሰብሳቢ አቶ የሺዋስ አሰፋ ናቸው።

በተያዘው ዓመት ይካሄዳል የተባለው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በአገሪቷ የመጀመሪያና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት የሚጣልበት ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።


የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የሱፍ ኢብራሂም በበኩላቸው ፓርቲያቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ችግር ምርጫ በማካሄድ ብቻ ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ።


ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ሁሉን ያማከለ ብሄራዊ ውይይትና ድርድር ማካሄድና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ለነገ የማይባሉ ተግባራት መሆናቸውን በማንሳት።


ፓርቲዎቹ በአገሪቷ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ያለው አማራጭ በሀሳብ ልዕልና መሸናነፍ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።


አገራዊ ምርጫው ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በእኩል ሜዳ ላይ የሚጫወቱበትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ጅማሮ ማሳያ እንዲሆን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ በበኩላቸው ቦርዱ ከተቋም ማደራጀት ጀምሮ አገራዊ ምርጫውን ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ ነው ይላሉ።


 የምርጫ ቁሳቁስ ዝግጅቱ  90 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ቀሪ 10 በመቶ ሥራዎች እስከ ድምፅ መስጫው ቀን ድረስ ይከናወናሉ ብለዋል።

የድምፅ መስጫ ቀኑ ሲቃረብ የድምጽ መስጫ ወረቀትና ለመራጮች ምልክት የሚደረግበት የማይለቅ ቀለም ግዥ እንደሚፈጸም አማካሪዋተናግረዋል።

በሌላ መልኩ ቦርዱ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን መረጃ በማጣራት ላይ መሆኑን አንስተው፣ እስካሁን ሙሉ መረጃ የላኩ የ78 ፓርቲዎች መረጃ እየተጣራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም