ቀጥታ፡

ሃዋሳ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የተለያዩ አገራት መሪዎችን የምትቀበል ከተማ እየሆነች ነው...ጠቅላይ ሚኒስትር

ሀዋሳ ሀምሌ 8/2010 ሃዋሳ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የተለያዩ አገራት መሪዎችን የምትቀበል ከተማ እየሆነች መምጣቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ገለጹ፡፡ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና የልዑካን ቡድናቸው በተዘጋጀ የእራት ግብዥ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ "በሲዳማ ሽማግሌዎች የሚከናወነው ባህላዊ የ‘ቄጠላ ስነስርዓት' ልብን የሚገዛ ነው" ብለዋል፡፡ የሲዳማ ህዝብ መልዕክቱን የሚያስተላለፍበት የቄጠላ ስነስርአት በሁሉም የደቡብ ከተሞች የሚሰማ የፍቅር ዜማ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ "በስነስርአቱ በመሸነፋችን ሃዋሳ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የተለያዩ የአገር መሪዎችን የምትቀበል ከተማ እየሆነች ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሃዋሳ ከተማና አካባቢዋ ህዝብ ውብ ከሆነው የቄጠላ ስነስርአት ጀምሮ ያደረገላቸው አቀባባል ልዩ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእዚህም መስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በአስመራና በአዲስ አበባ መካከል ግንኙነቱን ለማስቀጠል ግንቡ እንደፈረሰው ሁሉ በደቡብ አካባቢ ያሉ የሳርና ቄጤማ ግንቦች እንዲፈርሱም ጠይቀዋል፡፡ "የሚገባን፣ የሚበጀን የሚሆንልን ፍቅርና ሰላም ብቻ ነው" ያሉት ዶክተር አብይ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ወንድማማችነት የጋረደው ጥቁር መጋረጃ ብቻ መሆኑንና ይህም መቀደዱን ተናግረዋል፡፡ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው "የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ በደምና በአጥንት የተሳሰረ አንድ ህዝብ ነው" ሲሉ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በመድረኩ የመሀሙድ አህመድን የሰላም ዜማ ካቀረቡ ህጻናት መካከል ህጻን ስጦታው አጥናፉ እንደገለጸው በሁለቱ አገራት መሪዎች ፊት ቀርቦ የሰላም ዜማ በማቅረቡ መደሰቱን ገልጿል፡፡ "እኛ ህጻናት ሰላማዊ የሆነች አገር ስለሚያስፈልገን ኢትዮጵያና ኤርትራ ያካሄዱት ሰላም መድረክ ለሃገር ተረካቢው ትውልድ ጠቃሚ ነው" ብሏል፡፡ በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት በሙሉ ፍላጎታቸው እንደሆነ የገለጹትና ከአርሲ ኮፈሌ አካባቢ የመጡት አቶ ቁፋ ቆቤ በበኩላቸው፣ "በሃዋሳ የአገር ሽማግሌዎች እንግዶች ያደረጉት ባህላዊ አቀባበል እጅግ ልብ የሚነካና የሚያስደስት ነው" ብለዋል፡፡ "አገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ሰላም ተጠቅመንና በስራ ተደምረን  ለኢትዮጵያ እድገት እንሰራለን" ያሉት አስተያየት ሰጪው መንግስት ወጣቱን ኃይል በአግባቡ እንዲጠቀም ጠይቀዋል፡፡ ሰላምና ልማት የሚፈልግ ሰው ሁሉ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቱን ወደ እሳት ሳይሆን ወደ ሥራ እንዲመጣ የመምከር ኃላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ "ሁለቱ ህዝቦች አንድ ሆነን ተፈጥረን በመካከላችን በተፈጠረ ግጭት ተለያይተን ብንቆይም በሚያሸንፍ የፍቅር ልብ ተመልሰን ተዋህደናል፤ ወደ አስመራ ለመብረርና ዘመዶቻችን ለማግኘት ጓጉተናል " ብለዋል፡፡ በእራት ግብዣ መርሀ ግብሩ ላይ የክልሉን ህዝብ የሚገልጽ ባህላዊ አልባሳት ለሁለቱ አገራት መሪዎች የተበረከተላቸው ሲሆን የሲዳማ ዞንም በአገር ሽማግሌዎች በኩል ተጨማሪ ስጦታዎችን አበርክቷል ፡፡                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም