ለጎንደር ከተማና አጎራባች ዞኖች ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በትጋት እንሰራለን - የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለጎንደር ከተማና አጎራባች ዞኖች ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በትጋት እንሰራለን - የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች
ጎንደር ጥቅምት 1/2013 (ኢዜአ) - በጎንደር ከተማና በአካባቢው በሚገኙ አጎራባች ዞኖች የሰፈነውን አንጻራዊ ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
የጎንደር ከተማና አጎራባች ዞኖችን ሰላም በዘላቂነት ለማሰቀጠል የሚያግዝ የሰላም ውይይት ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ተሳታፊ የሆኑ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንደተናገሩት ሰላም የሁሉም ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ከአሁን ቀደም ለሰላም ያደረጉትን ጥረት በአዲሱ ዓመትም አጠናክረው ለመቀጠል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባት የሆኑት አባ ዮሴፍ ደስታ ሕዝቦች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ ሰላምና ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጠው የሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎት ነው።
የአካባቢው የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ባለፉት ዓመታት በጎንደር ከተማና በአጎራባች ዞኖች ተፈጥሮ የነበረው ግጭትና ብጥብጥ በሰላማዊ መንገድ በዕርቅና በሽምግልና እንዲፈታ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
''ዛሬ በአካባቢያችን መልካም የሚባል የሰላም ድባብ ተፈጥሯል ይህን ማስቀጠል የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል” ያሉት ደግሞ ከምዕራብ ጎንደር ዞን የመጡት የሀገር ሽማግሌ አቶ ወረቀት አያሌው ናቸው።
አሁን ላይ በአካባቢው የሰፈነውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል መንግሥት የሕግ የበላይነትን በማስፈን በኩል የጀመረውን ጥረት ሊያጠናክር እንደሚገባ ተናግረዋል።
“ከሰሜን ጎንደር የመጡት ቄስ ዓለሙ ቢያድግልኝ በበኩላቸው ሰላም በአንድ ወገን ጥረትና ፍላጎት ሊሰፍንና ቀጣይነትም ሊኖረው ስለማይችል ከመንግሥት ጋር ሆነን ሰላሙን በጋራ ለማስቀጠል እንሰራለን” ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ አግማስ በጎንደር ከተማና አካባቢው የሰፈነው አንጻራዊ ሰላም ለጎንደር የኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ ከ230 በላይ ባለሀብቶች ወደ ከተማው መምጣታቸውን ገልጸው ከተማ አስተዳደሩ በዚህ ዓመት ለአካባቢው ሰላም መጠናከር ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ባንቲሁን መኮንን በበኩላቸው እንደገለጹት በዞኑ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ በማድረግ በኩል የሁሉም አካላት የተቀናጀ ርብርብ አስፈላጊና ወቅታዊ ነው።
መስተዳድሩ ከውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች የተገኙ ግብአቶችን በመጠቀም የዞኑን ሰላምና የሕዝቡን ደህንነት ቀጣይነት በማረጋገጥ ልማቱን ለማጠናከርና ለወጣቶችም ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
“ሕገወጥ የሰዎችና የጦር መሣሪያ ዝውውር እንዲሁም የኮንትሮባንድ ንግድ ለሰላም መደፍረስ በር የሚከፍቱ ተግባራት ናቸው” ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጎንደር ዞን የሰላምና የሕዝብ ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ እንዳለ ማሩ ናቸው።
“በዞኑ የተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ለእርሻ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረው፤ ለውጭ ገበያ ሊቀርብ የተዘጋጀውን የሰሊጥ ምርት ያለ አንዳች የፀጥታ ችግር ባለሀብቶች መሰብሰብ እንዲችሉ የፀጥታ መዋቅሩ ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ነው”ብለዋል።
ለግማሽ ቀን በተካሄደውና የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ጎንደር ከተማና ከሁሉም የጎንደር ዞኖች አስተዳደሮች ጋር በመተባበር በተዘጋጀው መድረክ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመከላከያና የፖሊስ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የየዞኖቹ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።