በጭፍራ ወረዳ ህገወጥ የጦር መሳሪያ በመደበቅ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
በጭፍራ ወረዳ ህገወጥ የጦር መሳሪያ በመደበቅ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተያዙ

ሰመራ ጥቅምት 1/2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የጭፍራ ወረዳ ፖሊስ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ደብቀው አግኝቻቸዋለሁ ያላቸውን ሁለት ተጠርጠሪዎች መያዙን አስታወቀ።
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር አብደላ ሁመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ የተያዙት ትላንት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ነው።
በጭፍራ ከተማ ድንገት በተካሄደ የቤት ለቤት ፍተሻ ግለሰቦቹ ከደበቋቸው የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር መያዘቸውን ተናግረዋል ።
በግለሰቦቹ መኖሪያ ቤቶች ተደብቀው ከተያዙ የጦር መሳሪያዎች መካከል አራት ክላሽንኮቨ ጠብመንጃና አራት ሽጉጦች እንደሚገኙበት ተናግረዋል ።
በተጨማሪም 2 ሺህ 289 የመትረየስና 112 የክላሽ ጥይቶች እንዲሁም 50 ባዶ የክላሽ ካርታና ሁለት የእጅ ቦምቦች መያዛቸውን ጠቅሰዋል ።
መሳሪያው የተገኘባቸው ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ገልጸዋል ።
የወረዳው ፖሊስ የጀመረውን ህገወጥ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።
ፖሊስ የህዝብና የሀገርን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ ህገወጥ እንቅስቃሴዎች ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ህብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዋና ኢንስፔክተር አብደላ ጠይቀዋል።