ቀጥታ፡

በወረባቦ ወረዳ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ዘጠኝ ሺህ ሄክታር የማሽላ ሰብል አወደመ

ጥቅምት አዲስ አበባ  1/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ዘጠኝ ሺህ ሄክታር የማሽላ ሰብል በማውደሙ አርሶ አደሩ ለችግር መጋለጡ ተገለጸ።

የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ መንጋውን ለመከላከል ከቀላል ኬሚካል መርጫ እስከ አነስተኛ አውሮፕላን ድረስ በማሰማራት የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ነው ብሏል።


የተከሰተው የአንበጣ መንጋ የአርሶ አደሮች ሕልውና መሰረት የሆነውን ማሽላ ሙሉ ለሙሉ እያወደመባቸው መሆኑን የወረዳው አርሶ አደሮች ለኢዜአ ተናግረዋል።

ደቡብ ወሎ ዞን መስከረም 15 አካባቢ በተከሰተ የአንበጣ መንጋ ክፉኛ እየተጎዱ ከሚገኙ ዞኖች መካከል አንዱ ነው።

በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል አንዱ የሆነው የወረባቦ ወረዳ ካሉት ከ20 ቀበሌዎች ውስጥ በ12ቱ ቀበሌዎች የተዘራው ማሽላ በመንጋው ተበልቷል።

በዚህ የአንበጣ መንጋ ወረራ የማሽላ ሰብሉ የወደመባቸው አርሶ አደር ሁሴን መሐመድ ስድስት አባላት ያለውን ቤተሰባቸውን ምን መመገብ እንዳለባቸው በመቸገራቸው ግራ ተጋብተዋል።

ከዚህ ቀደም የተሻለ ምርት ያገኙ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ በአንበጣ መንጋ ምክንያት ምርት ሊያገኝ እንደማይችሉና ሕይወታቸው ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት የ47 ዓመቱ ጎልማሳ አርሶ አደር አህመድኑር አብዱ በሕይወት ዘመናቸው እንዲህ አይነት ችግር አይተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

የአንበጣ መንጋ ወረርሽኙን በባህላዊ መንገድ የመከላከል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ውጤት እንዳላመጣና የአካባቢው ሰብል መውደሙን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ አርሶ አደር አብዱሽ አሊ መሐመድና አርሶ አደር መሐመድ ሱሩር አንበጣው ሕይወታቸውን ለአደጋ ማጋለጡን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ የሚሉት በቀጣይ በምግብ እህልም ይሁን በምርጥ ዘር መንግስት ከጎናቸው እንዲሆን ነው።

በወረባቦ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ አህመድ እሸቱ በበኩላቸው ላለፉት ሁለት ወራት የአንበጣው መፈልፈያ ቦታ ተለይቶ ርጭት ሲደረግ እንደነበር ገልጸዋል።

የመከላከል ስራው ሲሰራ የቆየ ቢሆንም ችግሩ ከአቅም በላይ በመሆኑ ጉዳት ማስከተሉን ጠቁመዋል።

በወረዳው ዘጠኝ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ የማሽላ ሰብል በሙሉ ከጥቅም ውጪ በመሆኑ 51 ሺህ አርሶ አደሮችን ለችግር እንደዳረገ አመልክተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ሰኢድ መንጋውን የመከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአምስት ሺህ በላይ ቀላል የእጅ ኬሚካል መርጫ መሳሪያ መሰራጨቱን ገልጸዋል።

''ከ68 በላይ ሞተር ያላቸው መርጫ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እየዋለ ነው'' ያሉት አቶ አሊ፤ 15 ሺህ ሊትር በላይ ኬሚካል ለርጭት መዘጋጀቱንና በአነስተኛ አውሮፕላን ጭምር የታገዘ ርጭት እየተካሄደ እንደሆነ አብራርተዋል። 

አቶ አሊ እንደሚሉት፤ በዞኑ በዚህ ዓመት 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት 400 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኖ ነበር።

ምንም እንኳን በዚህ ወቅት አንበጣው በወረባቦና አርጎባ ወረዳ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ቢሆንም ባለፈው ነሐሴ ወር ግን በዞኑ 13 ወረዳዎች ላይ መከሰቱን ያስታውሳሉ።

በመሆኑም በዚህ ዓመት የታሰበው ያህል ምርት ሊገኝ ስለማይችል አርሶ አደሩ ለረሃብና ለስደት እንዳይዳረግ ለመደገፍ የሚያስችል ስራ ለመስራት ዕቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

የአንበጣ መንጋ ከደቡብ ወሎ ዞን በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎችም ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም