ቀጥታ፡

አስጎብኚ ድርጅቶችና ሆቴሎች ሥራቸውን በተጠናከረ መልኩ ለመጀመር መዘጋጀታቸውን ገለፁ

አዲስ አበባ፣መስከረም 30/2013 (ኢዜአ) መንግሥት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተጎዳውን ቱሪዝም እንዲያገግም በሩን ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ መወሰኑን ተከትሎ አስጎብኚ ድርጅቶችና ሆቴሎች ሥራቸውን ለመጀመር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በዓለም የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ያሳረፈው ጉዳት ''ከፍተኛ'' መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍም በወረርሽኙ ከተጎዱት ዘርፎች አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎችም፤ የኢትዮጵያ ቱሪዝም በወረርሽኙ የደረሰበት ጉዳት ቀላል እንዳልሆነ ተናግረዋል። 

የአድማሱ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት አቶ አድማሱ ገበየሁና የባለሀገሩ አስጎብኚ ድርጅትሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ አየለ ኮቪድ-19 ባስከተለው  ጉዳት ገቢያቸው መቀነሱን ገልጸዋል።

ቢሮ እስከ መዝጋትና የሠራተኞቻቸውን ቁጥር እስከ መቀነስምመድረሳቸውንም ጠቅሰዋል። 

የካሌብ ሆቴል ምክትል ሥራ አስኪያጅ ጌታ ብቻ ደጀኔ በበኩላቸው በኮቪድ-19 ምክንያት በቀን የሚከራዩ አልጋዎች መጠን ከ10 በመቶ በታች እንደወረደ ይናገራሉ። 

ዘርፉ እንዲያገግም መንግሥት እየወሰደ ባለው እርምጃ ብሔራዊ የደህንነት መጠበቂያ ፕሮቶኮል ማዘጋጀቱን የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ አስታውቀዋል። 

ከነዚህም ውስጥ ጎብኚዎች ከኮቪድ-19 ስጋት ነፃ ሆነው ከጥቅምት ወር ጀምሮ አገሪቱን እንዲጎበኙ ማድረግ ይጠቀሳል። 

አስጎብኚዎችና ሆቴሎችም ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት መንግሥት ዘርፉን ለማነቃቃት የሰጠውን ውሳኔ አድንቀዋል። 

ውሳኔው ከጉዳታቸው እንዲያገግሙና ዘርፉን ለማሻሻል አስተዋፅኦ ለማድረግ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል። 

መንግሥት ያወጣቸውን የኮቪድ-19 መከላከያ መመሪያዎችን በመተግበር ለእንግዶቻቸው ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት እንደሚሰሩም አስታውቀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም