የእንጦጦ ፓርክ አፍሪካ የቱሪዝም ሃብቷን ለስራ ፈጠራ ማዋል እንዳለባት አብነት የሚሆን ፕሮጀክት ነው - አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የእንጦጦ ፓርክ አፍሪካ የቱሪዝም ሃብቷን ለስራ ፈጠራ ማዋል እንዳለባት አብነት የሚሆን ፕሮጀክት ነው - አምባሳደሮች
አዲስ አበባ መስከረም 30/2013 (ኢዜአ) የእንጦጦ ፓርክ አፍሪካ ያላትን የቱሪዝም ሃብት ለስራ ፈጠራ ማዋል እንዳለባት አብነት የሚሆን ፕሮጀክት ነው ሲሉ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ከተማ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአዲስ አበባ የተገነባውን የእንጦጦ ፓርክ ዛሬ መርቀው ለሕዝብ ክፍት አድርገዋል።
የፓርኩን ዋና ዋና ስራዎች ለማጠናቀቅ ሰባት ወራትን ብቻ የወሰደ ሲሆን በውስጡም ግዙፍ የስነ-ጥበብ ጋለሪ፤ አምፊ ቲያትር፣ የተለያዩ መዝናኛዎችና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ይዟል።
የፓርኩ ለጉብኝት ክፍት መሆን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተጎዳውን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ እንዲያገግም በማድረግ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትም ዛሬ ፓርኩን ጎብኝተዋል።
በኢትዮጵያ የቡርኪናፋሶ አምባሳደር ሊዮፖልድ ቶንግኖማ የቱሪዝም ሴክተሩ በአፍሪካ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ጉልህ ሚና ሊኖረው ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በዘርፉ የተሻለ ሀብት ያላት አገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞም የእንጦጦ ፓርክ ፕሮጀክት ለዘርፉ መጎልበት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
ፓርኩ የአፍሪካ አገራት ከኢትዮጵያ ልምድ ወስደው መሰል ተግባር እንዲያከናውኑ መነሳሳት እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፌል ሞሮቭ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዲፕሎማቲክ መቀመጫ እንደመሆኗ የአህጉሩ ቱሪዝም ማዕከል መሆን እንደሚጠበቅባት ገልጸዋል።
ከዚህ አንጻር አዲስ አበባን ለማስዋብ እየተከናወነ ያለው ተግባር ለአገሪቷ ቱሪዝም ዕድገት ትክክለኛ መንገድ መሆኑን ነው ያስረዱት።
በተለይ ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ካላት እምቅ ሃብት አንጻር ዘርፉ የዕድገት ሞተር እንዲሆን በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብርቱካን አያኖ በርካታ የአፍሪካ አገራት በተፈጥሮ ሀብት የበለጸጉ መሆናቸውን አውስተዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ አዲስ አበባ የዲፕሎማቲክ መዲና መሆኗ ደግሞ የአፍሪካ መሪዎች ፕሮጀክቱን የመጎብኘት ዕድል እንዲኖራቸው ያደርጋል።
በመሆኑም ፕሮጀክቱ በአፍሪካዊያን መካካል ልምድ እንዲሰፋ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
በአዲስ አበባ የሚኖሩ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰን አባላት ለጉብኝት ወደሌላ አገር በማቅናት የሚያጠፉትን ጊዜ እንደሚቆጥብም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በተለይ በኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ዘንድ የ'ይቻላል መንፈስ' እንደሚፈጥርም ጨምረው ገልጸዋል።
በእንጦጦ ፓርክ ቀድሞ በአካባቢው እንጨት በመልቀም ለሚተዳዳሩ ከ460 በላይ እናቶች የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።