ቀጥታ፡

ለሕክምና ባለሙያዎች እውቅና የሚሰጥ ሐውልት መቆሙ ትልቅ አቅምና የሞራል ስንቅ የሚፈጥር ነው ... ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፣መስከረም 30/2013 (ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እየሰሩ ላሉ የሕክምና ባለሙያዎች የእውቅና ሐውልት መቆሙ ለባለሙያዎቹ ትልቅ አቅምና የሞራል ስንቅ እንደሚፈጥርላቸው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ የእንጦጦ ፓርክን መርቀው ለሕዝብ ክፍት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ላሉ የሕክምና ባለሙያዎች እውቅና የሚሰጥ ሃውልት በፓርኩ ውስጥ መርቀዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ መንግስት የኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ ወረርሽኙን ለመከላከል በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ነው ለኢዜአ የተናገሩት።

በዚህ ጥረት ላይ ደግሞ የሕክምና ባለሙያዎች የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ጭምር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።

ለዚህ ጥረታቸው እውቅና ለመስጠት በፓርኩ ውስጥ ሃውልት እንዲቆምላቸው መደረጉንም ነው የገለጹት።

ለሕህክምና ባለሙያዎቹ የተሰጠው እውቅናም በቀጣይ ወረርሽኙን ለመከላከል ለሚያከናውኑት ተግባር ከፍተኛ ተነሳሽነት እንደሚፈጥርላቸውም ሚኒስትሯ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የእንጦጦ ፓርክ ከመስህብነት ባሻገር ጤናን ለመጠበቅ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ በሚያስችል መልኩ መገንባቱን ነው ያስረዱት።

ይህም በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቀነስ አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በበኩላቸው የሕክምና ባለሙያዎች ባደረጉት አኩሪ ተጋድሎ በኢትዮጵያ ወረርሽኙ የተፈራውን ያህል ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የሕክምና ባለሙያዎች በዚህ ፈታኝ ወቅት ለአገራቸው ካከናወኑት ተግባር አንጻር እውቅና እንደሚገባቸው ገልጸው፤ የሀውልቱ መቆም ለቀጣይ ስራ ሞራል እንደሚሆናቸው ጠቅሰዋል።

መንግስት ለሕክምና ባለሙያዎች ለሰጠው እውቅና ዶክተር ኤባ ምስጋና አቅርበዋል።

መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ከቡርኪናፋሶ የመጣ ጃፓናዊ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተያዘ የመጀመሪያው ግለሰብ ሲሆን፤ እስከ ትናንት ባለው መረጃም 82 ሺህ 662 ሰዎች ኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፤ 1 ሺህ 271 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፤ 37 ሺህ 102 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 1 ሚሊዮን 335 ሺህ 856 የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም