"መስከረም 30 የኢትዮጵያዊነት ድምጽ" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሠላማዊ ሠልፍ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
"መስከረም 30 የኢትዮጵያዊነት ድምጽ" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሠላማዊ ሠልፍ ይካሄዳል
አዲስ አበባ መስከረም 30/2013 (ኢዜአ) በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን "መስከረም 30 የኢትዮጵያዊነት ድምጽ" በሚል መሪ ቃል ዛሬ ሠላማዊ ሠልፍ ያካሂዳሉ።
ዓለም አቀፍ የዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ ዓለማየሁ አበበ
ሠላማዊ ሠልፉ 'ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት አይኖርም፤ ኢትዮጵያ አትቀጥልም ትፈርሳለች' የሚሉ አካላትን ለመቃወም የተዘጋጀ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በሠላማዊ ሠልፉ "ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች፣ ኢትዮጵያ ትኖራለች የሚሉና ኢትዮጵያዊነትን የሚያወድሱ መልዕክቶች እንደሚተላለፉ ተናግረዋል።
ሠላማዊ ሠልፎቹ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮጳና በአውስትራሊያ በሚገኙ ከተሞች እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ እንደሚካሄዱም ነው አቶ ዓለማየሁ ያስረዱት።
አትላንታ ጆርጂያ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዳላስ ቴክሳስ፣ ሲያትል፣ ዋሽንግተን ዲሲና ሜኒሶታ ግዛቶች ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሠላማዊ ሠልፉ በአካል እንደሚወጡም ጠቁመዋል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በተጣሉ ገደቦች በላስቬጋስ ፣ ኔቫዳ እና በዴንቨር ኮሎራዶ በይነ መረብና ሌሎች የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አማራጮችን በመጠቀም ሠላማዊ ሠልፉ ይካሄዳል ብለዋል።
በአውሮጳ በእንግሊዝ፣ በኢጣሊያና ኖርዌይ፣ በካናዳ ቶሮንቶ፣ በአውስትራሊያና ደቡብ አፍሪካ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መመሪያ ታሳቢ በማድረግ በአካልና በበይነ መረብ ሠልፉ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ ሰልፎቹ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጡ መመሪያዎችን በመከተል እንደሚካሄዱም ነው ያስረዱት።
"መንግስት ይመጣል መንግስት ይሄዳል፤ ሰዎች ይመጣሉ ሰዎች ይሄዳሉ፤ ኢትዮጵያ ግን ትቀጥላለች" ያሉት አቶ ዓለማየሁ ሁሉም ዜጋ ለኢትዮጵያ አንድነትና ዕድገት በጋራ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።
የትኛውም አካል ከኢትዮጵያ በላይ ሊሆን ስለማይችል ይህን ባገናዘበ መልኩ ሁሉም በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
በሠላማዊ ሠልፉ የሚሳተፉ ዜጎች ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ከሠልፉ ዓላማ ውጭ የሆኑ ተግባራትን ከመፈፀም እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
ሠልፉ በዓለም አቀፍ የዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤትና በየከተሞቹ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
ምክር ቤቱ ከስድስት ወራት በፊት የተቋቋመና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ድምፅ የማሰማትና ዕድገትና ልማቷን የሚደግፉ ስራዎችን የማገዝ ዓላማ ያለው እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጉዳዮች ጫናዎች እንዳይደርሱባት ተጽዕኖ የመፍጠር /ሎቢ/ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም አክለዋል።
ምክር ቤቱ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮጳና አውስትራሊያ አህጉራት እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ዜጎችና በኢትዮጵያዊያን የተቋቋሙ ድርጅቶችን ያስተባበረ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።
በቀጣይ የምክር ቤቱ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ይፋ ለተደረገው የ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በበይነ መረብ ምክክር እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።
በምክር ቤቱ በኩል ፕሮጀክቱን የመደገፍ ፍላጎት እንዳለም አስታውቀዋል።