ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ምሁራን ገለጹ

ሀዋሳ መስከረም 30/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሃገሪቱን ዕድገት ለማስቀጠልና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን ገለጹ።

በዩኒቨርሲቲው የስምጥ ሸለቆ ጥናትና ምርምር ማዕከል የባዮ ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ምህረት ደናንቶ እንዳሉት ግድቡ ሲጠናቀቅ  የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት በእጥፍ በማሳደግ  አሁን ያለውን እጥረት ለማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ይህም በእያንዳንዱ ዜጎች  ህይወት ላይ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ ነው ያሉት ዶክተር ምህረት በተለይ በሥራ ፈጠራ የተሰማሩ  ዜጎችን የስራ ተነሳሽነት እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ዕድገት ለማስቀጠል፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠርና የዓሣ ሀብት ምርት መጠንን ለማሳደግ  ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ግድቡ የሃገሪቱን የቱሪዝም ፍሰትን  እንዲጨምር ያደርጋል ያሉት   ዶክተር ምህረት  ግብርናውንም ለማዘመን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ አስረድተዋል።

የአባይ ወንዝ መነሻና ባለቤት የሆነች ኢትዮጵያ በፍትሃዊነት መርህ ለመጠቀም ወደ ተግባር መግባቷ ለዘመናት የታችኞቹ ሃገራት ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር የሞከሩት በመቀየር በተለይም የላይኞቹ የተፋሰስ ሃገራት የመደራደር አቅማቸው ከፍ እንዲል ያደርጋል ብለዋል።

የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ለሀገሪቱና ዜጎቿ ክብር መሆኑን የገለጹት  ዶክተር ምህረት ግድቡ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲበቃ  ሁሉም የተቻለውን እንዲደግፍም ጠይቀዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ውሃ ሀብትና መስኖ ምህንድስና  ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ አሰፋ በበኩላቸው ግድቡ ሲጠናቀቅ አስተማማኝ የኤልክትሪክ ኃይል ምንጭ ይፈጥራል ብለዋል።

የዓለም አቀፍ ቀጥታ ኢንቨስትመንት  በመሳብ ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራን ከማስፋት ባለፈ የውጭ ምንዛሬን በማዳን ረገድም ሚናው የጎላ  መሆኑን ተናግረዋል።

ግብርናውን በማዘመን በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ከማድረግ ረገድ የሚጫወተው ሚና ወደር የለውም ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ መላውን ዜጎችን ያሳተፈ በመሆኑ ለሃገራዊ አንድነትና መግባባትም የሚኖረው ሚና የላቀ መሆኑን የጠቀሱት ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ በቀጠናውም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ተሰሚነት ከፍ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ገብቶ ግንባታው መጓተቱ ለውጭው ብቻ ሳይሆን በሃገር ውስጥ ለተፈጠሩ አለመረጋጋቶች አስተዋጽኦ እንደነበረም አንስተዋል።

ከዲዛይን እስከ ግንባታ ግብዐት አቅርቦት ድረስ የገጠሙ ችግሮች ተስተካክለው የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ መቻሉ ከፍተኛ የሆነ የደስታ ስሜትና መነሳሳት መፍጠሩን አስረድተዋል።

ግድቡ ፍፃሜ አግኝቶ ለውጤት  እንዲበቃ  በየደረጃው የተጀመረው ድጋፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተፅዕኖ የመፍጠር ሥራ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም