ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የፋይናንስና መሰል ኢኮኖሚያዊ በሯን ለዳያስፖራና ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት በማድረግ ላይ ነች

አዲስ አበባ መስከረም 30/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ነፃ በማድረግ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በጀመረችው ጉዞ ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ የተፈቀዱ ዘርፎችን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ ጀምራለች።

አዲሱ አዋጅ በአገሪቷ በፈረንጆቹ 2020 መጀመሪያ አካባቢ የተሻሻለውን የኢንቨስትመንት አዋጅ መሰረት በማድረግ የውጭ አገር ዜግነት ላላቸው ኢትዮጵያዊያንና ለውጭ አገራት ዜጎች እኩል ተጠቃሚነትን አረጋግጧል ሲል አፍሪካ ሪፖርት ዘግቧል።

ካናዳዊ ዜግነት ያላቸውና በካናዳ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኢንቨስተሩ አዲስ አለማየሁ "በተወለድንበት አገር ያለንን ሃብት እንድናፈስ ፈቃድ ማግኘታችን ብዙ አማራጮችን ያስገኝልናል" ሲሉ ተናግረዋል።

ዳያስፖራዎች በአገራቸው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እያበረታታች ቢሆንም በምዕራቡ አገራት የሚኖሩ አንዳንድ አክቲቪስቶች ነገሩን ወደኋላ ለመጎተት እየሰሩ መሆኑም ተጠቅሷል።

"አገሪቷ ንግድ ባንኮች ውስጥ ያለንን ድርሻ እንኳን እንዳንሸጥ ተከልክለን ነበር፤ መንግስትም መብታችንን ገድቦት ቆይቷል አሁን ግን በባንኮች ድርሻ ለመያዝና ለመሸጥ ተፈቅዶልናል" በማለት በኢንተርኔት ንግድ ላይ የተሰማራችው ቤተልሄም ሰይፉ ገልፃለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በነበሩት ሁለት ዓመታት ዳያስፖራው በኢኮኖሚው ውስጥ እያደረገ ያለው ተሳትፎ በእጅጉ ጨምሯል።

በውጭ በሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መስራችነት በ400 ሚሊዮን ዶላር ሁለት የግል ባንኮች በምስረታ ላይ እንደሚገኙም ተጠቅሷል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በዓማካይ ወደ አገሪቱ በሃዋላ የሚላከው ገንዘብ 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ይህም ከዚህ በፊት ከነበረው በ4 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ያለ መሆኑ ተመልክቷል።

"ዳያስፖራው ህጋዊ የባለቤትነት ፈቃድ በማግኘቱ በቀጣይ ዓመታት በፋይናንሱ ዘርፍ በንቃት እንደሚሳተፍ ይጠበቃል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ አዳዲስ የባንክ ዘርፎችን እየተመለከትን ነው፤ ዳያስፖራውም ባለድርሻ በመሆን ወደ ዘርፉ እየገባ ነው" በማለት ታዋቂው የኢንቨስትመንት አማካሪ ዘመዴነህ ንጋቱ ለመጽሄቱ ገልጸዋል።

በአዲሱ አዋጅ መሰረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት የሆኑ ዘርፎች የተለዩ ሲሆን ይህን ተከትሎ የሲሚንቶ ዘርፍም ለውጭ አገር ዜጎች ክፍት መደረጉ ተጠቅሷል።

"በአገሪቱ የሲሚንቶ ዘርፍ ለመሰማራት የተፈቀደለት የመጨረሻው የውጭ ኩባንያ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ነበር፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረት ቢታይበትም ለማንኛውም አዲስ ፈቃድ ጠያቂ ይሁንታ አይሰጥም ነበር" በማለት በኬሚካልና ኮንስትራክሽን እቃዎች አቅራቢ ልማት ኢንስቲትዩት የሲሚንቶና ተያያዥ ኢንዱስትሪዎች ልማት ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ስመኝ ደጉ ተናግረዋል።

"አዲሱ ፈቃድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቷ የሚታየውን የሲሚንቶ እጥረት ከስሩ ለመቅረፍ ሁነኛ መፍትሄ ነው" ብለዋል።

በአዲሱ አዋጅ መሰረት የሎጂስቲክ ዘርፉም በከፊል ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ተደርጓል።

በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ የውጭ አገር ተወላጆች ከኢትዮጵያዊያን ጋር በአክሲዮን ድርሻ የሚጣመሩ ሲሆን ድርሻቸው ከ51 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ተደንግጓል።

የፕሪሳይዝ አማካሪ ድርጅት የኢንቨስትመንት አማካሪ ሄኖክ አሰፋ "የሎጂስቲክ ዘርፉ የአገሪቱ ዋነኛ ፈተና ነው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዳንሆን ያደረገን ዋነኛ ማነቆ ይኽው ነው፤ ዘርፉን ሙሉ በሙሉ ክፍት ማድረጉ በጣም የተሻለ አማራጭ ነው፤ በዘርፉ ያለንን አቅም ለማሳደግ የውጭ ካፒታልና እውቀት በጣም አስፈላጊ ነው" ይላሉ።

የንግድ ምቹነትን የሚቃኘው Doing Business 2020 ባወጣው መረጃ በአገሪቷ የውጪ ንግድ ዶክመንትን ለማረጋገጥ 194 ሠዓት የሚፈጅ ሲሆን በድንበር አካባቢ ለመነገድ የሚያስችለውን ሰነድ ለማረጋገጥ ደግሞ 74 ሰዓት ይወስዳል።

ወደ ውጭ ለሚላክ ምርት ሰነድ ማረጋገጫ የሚከፈለው 750 ዶላር በሩዋንዳ ከሚጠየቀው ሶስት እጅ የበለጠ መሆኑን ተቋሙ በጥናቴ አረጋግጫለሁ ብሏል።

በሎጂስቲክ ዘርፉ ያለው ውጣ ውረድ የውጪ ንግድ ላኪዎችን ተስፋ ያስቆረጠ ሲሆን የኢትዮጵያ የውጪ ሸቀጦች ውድ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ከትክክለኛ የመሸጫ ዋጋው ሶስት እጅ የላቀ ዋጋ እንዲጠይቁ ያደርጋቸዋል።

መስከረም 21 ቀን 2013  በመጀመሪያው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ፖሊሲ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉንና በአዋጁ በመታገዝ የመልቲ ሞዳል ዘርፉን ለግል ባላሃብቶች ክፍት ለማድረግ ጉዳዩን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላካቸውን የባህር ትራንስፖርት ጉዳዮች ባለስልጣን ዳይሬክተር ጄኔራል መኮንን አበራ ተናግረዋል።

አዋጁ በተጨማሪ የኃይል ዘርፉን ሙሉ በሙሉ ክፍት ያደረገ ቢሆንም በኤሌክትሪክ የውጪ ንግድ ላይ መሰማራት የሚሹ የውጭ ባለሃብቶች ግን ከመንግስት ጋር በሽርክና መስራት አለባቸው ይላል።

በአዲሱ አዋጅ መሰረት የውጭ ባለሃብቶች ኤሌክትሪክ በማመንጨትና በማከፋፈል ላይ መሰማራት ይችላሉ። 

በአዲሱ አዋጅ የትራንስፖርት ዘርፉም ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ተደርጓል።

በዚህም የውጭ ባለሃብቶች በአየር፡ በባቡር በመርከብና በጭነት አገልግሎት ላይ ኢንቨስት በማድረግ መሰማራት ይችላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ባለሃብቶቹ በማስታወቂያ፣ በኦዲዮቪዥዋል አገልግሎት፣ በተንቀሳቃሽ ፊልምና ቪዲዮ ቀረፃ፣ ፕሮዳክሽንና ስርጭት፣ በሂሳብ ስራና በኦዲት አገልግሎት መሰማራት የሚችሉ ሲሆን ድርሻቸው ግን ከ49 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ተደንግጓል።

የፋይናንስ ዘርፉ አሁንም ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ ሲሆን ይህም የአገር ውስጥ ባንኮችን ለመጠበቅ የተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የአገር ውስጥ ባንኮችን ማጠናከርና ለወደፊቱ ከውጭ ባንኮች የሚጠብቃቸውን ፉክክር ለመቋቋም ማዘጋጀቱ ዘርፉ ክፍት ሲደረግ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው ዘመዴነህ ንጋቱ ተናግረዋል።

በአገሪቷ የሚገኙት 16 የግል ባንኮች ጠንካራ ወደሆኑ 4 ወይም 5 ግዙፍ ባንኮች ቢለወጡ አዋጪ መሆኑንም መክረዋል።

"ለመወዳደር ጠንካራ የገንዘብ አቋም ሊኖርህ ይገባል" ሲሉ አማካሪው ምክራቸውን አስቀምጠዋል።

"የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ክፍት መደረጉ አይቀርም፣ በአዕምሯችን መያዝ ያለብን አንዱ ጉዳይ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ካሳዩ ዓለም ዓቀፍ ባንኮች መካከል የኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጀሪያ ባንኮች እንደሚገኙበት ነው" ሲሉ አብራርተዋል።

በአሜሪካና አውሮፓ የሚገኙ ምዕራባውያን ባንኮች ወደ አፍሪካ የመስፋፋት ፍላጎት የላቸውም፣ አሁን ላይ አነስተኛውን የባንክ ንግድ በመተው ከበርካታ የአፍሪካ አገራት እየወጡ ነው፤ ትኩረታቸውንም በኮርፖሬት ባንኪንግ ላይ አድርገዋል ብለዋል።

ባርክሌይን የመሰሉ ግዙፍ ባንኮች ከአፍሪካ ሙሉ በሙሉ ለቀው ወጥተዋል ሲሉ የዝግጅቱን አስፈላጊነት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም