በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ የ4 ሕፃናት ሕይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ የ4 ሕፃናት ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ መስከረም 30/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ በተለምዶ አየር አምባ በሚባለው አካባቢ በደረሰ የእሳት አደጋ የ4 ሕፃናት ሕይወት አለፈ።
በእሣት አደጋው አንድ ሰው ቆስሏል 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትም ወድሟል።
የአዲስ አበባ እሳት አደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት የቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ትናንት ማምሻውን 1 ሠዓት ከ35 ደቂቃ አካባቢ በተከሰተው የእሳት አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው ሕፃናትና ታዳጊ ቤተሰቦቻቸው በር ቆልፈውባቸው በመሄዳቸው ከአደጋው ማምለጥ እንዳልቻሉ ገልፀዋል።
በቃጠሎው ሕይወታቸው ያለፈው የዘጠኝ ወር ህጻን ሴት፣ የ4 እና 14 ዓመት ሴቶች እና የአምስት ዓመት ወንድ ልጆች መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ሕይወታቸው ካለፉት ሰዎች ጎረቤት የምትገኝ የ19 ዓመት ሴትም ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባታል።
አደጋው የተከሰተው በሱቆች ውስጥ እንደሆነና ቃጠሎው ወደ መኖሪያ ቤቶች መዛመቱን ነው አቶ ጉልላት ያስረዱት።
ሱቆቹና መኖሪያ ቤቶቹ የተጠጋጉ በመሆናቸው እሳቱ በፍጥነት ተዛምቷል ነው ያሉት።
በሰው ህይወት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በስድስት ሱቆችና በመኖሪያ ቤቶች ላይ በደረሰው አደጋ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ገልጸዋል።
47 የእሳት አደጋ ሰራተኞች ከሁለት ሰአት በላይ ባደረጉት ርብርብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን ተችሏል ብለዋል።
የአደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ እንደሚገኝና የምርመራው ውጤት ሲታወቅ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ አመልክተዋል።
በግንቦት 2012 ዓ.ም በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በእንጨትና ችቡድ ማምረቻ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ያስታወሱት አቶ ጉልላት በእሳት አደጋ የሰዎች ሕይወት የሚያልፈው ከአደጋው ለመሸሽ ማምለጫ በማጣት እንደሆነና የትናንት ምሽቱ አደጋ የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።
ቤተሰቡ በህጻናትና በታዳጊዎች ላይ በር ቆልፈው መሄድ እንዳልነበረባቸው የገለጹት አቶ ጉልላት ህጻናትና አዛውንት ላይ በር ቆልፎ መሄድ ለእንደዚህ አይነት አስከፊ አደጋ ያጋልጣል ብለዋል።
ከፍተኛ ጥግግት ባላቸው ቤቶች አካባቢ ተቀጣጣይ ነገሮችና የኤሌክትሪክ መስመር ቅጥልጥሎሽ ብዙ ጊዜ የእሳት አደጋ እንደሚያደርስ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ እሳት አደጋ እና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለጉዳዩ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት የአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን የመለየት ተግባር እያከናወነ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ ባካሄዳቸው ጥናቶች ከፍተኛ የአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎችን ወደ ሌላ ቦታ የማዘዋወርና ባሉበትም ተጋላጭነታቸውን መቀነስ የሚያስችሉ ሁኔታዎች መፍጠር የሚሉ ምክር ሀሳቦችን ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረቡን ነው አቶ ጉልላት ያስረዱት።
ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡላቸውን ምክረ ሀሳቦች ተቀብለው ከመፈፀም አኳያ ድክመት እንዳለና ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።
ማህበረሰቡ የእሳት አደጋ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ራሱንና አካባቢውን ከአደጋ እንዲጠብቅ አሳስበው በእሳት አደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ህፃናት ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።
የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥም በነጻ የስልክ መስመር 939፤ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 011 155 53 00 ወይም በ011 156 86 01 ደውሎ ማሳወቅ እንደሚችልም ጠቁመዋል።