ሠራዊቱንም ሆነ የሠራዊቱን አመራሮች ስም ማጉደፍ የአገርን ክብር መንካት ነው - የቀድሞ ሰራዊት ጦር መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱንም ሆነ የሠራዊቱን አመራሮች ስም ማጉደፍ የአገርን ክብር መንካት ነው - የቀድሞ ሰራዊት ጦር መኮንኖች
አዲስ አበባ ፣መስከረም 29/2012 (ኢዜአ) የመከላከያ ሠራዊቱን እና የሠራዊቱን አመራሮች ስም ማጉደፍ የሀገርን ክብር መንካት ነው ሲሉ የቀድሞ ሰራዊት ጦር መኮንኖች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ዘመናትን በተሻገረ የነጻነት ታሪኳ ውስጥ በየጦር ሜዳው የተከፈለው መስዋትነት ትልቁን ድርሻ ይይዛል።
በአሁኑ ትውልድም ሰራዊቱ የአገርን ህልውናና የዜጎችን አብሮነት የሚፈታተኑ የውጭም ሆነ የውስጥ ሴራዎችን በመከላከል ረገድ አኩሪ ታሪኮችን እየጻፈ ይገኛል።
"ከራስ በላይ ለአገርና ለህዝብ" የሚለው እሴት ደግሞ ሰራዊቱ የተገነባበት ማንነት ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹምና የኦፕሬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በቅርቡ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ያረጋገጡት ይህንኑ ነው።
ጄኔራሉ በዚህ ወቅት ሰራዊቱ ያለምንም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የአገር ህልውናንና ህገ-መንግስቱን በማስጠበቅ ረገድ አሁንም ዝግጁ ነው ብለዋል።
በመሆኑም "ህገ-መንግስቱን በጣሰ መልኩ በኃይል ፍላጎቴን አሳካለሁ በሚል ማንኛውም አካል ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተከናወነው ሪፎርም ሰራዊቱ የትኛውንም ግዳጅ የመፈጸም አቅሙን እንዳጎለበተውም ጀኔራሉ መናገራቸው ይታወሳል።
በሰራዊቱ ውስጥ ጠንካራ ውስጣዊ አደረጃጃት በመኖሩ በየትኛውም አካል የሚነዛ ውዥንብር በሰራዊቱ ዘንድ ቦታ እንደሌለውም ነው በወቅቱ ያስረዱት።
የጄኔራሉን ሃሳብ ተከትሎም አንዳንድ አካላት የመከላከያ ሠራዊቱን እና የሠራዊቱን አመራሮች ስብዕና የሚያጎድፉ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን እያካሄዱ ይገኛሉ።
አብዛኛዎቹ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ደግሞ ዘለፋ አዘል ናቸው።
የቀድሞ ሰራዊት የአየር ወለድ ጦር መኮንኖች በሰራዊቱ አመራሮች ላይ የሚደረገው የስም ማጥፋት ዘመቻ እውነታ የሌለውና ከጥላቻ የመነጨ መሆኑን ነው ለኢዜአ የተናገሩት።
የቀድሞ ሰራዊት አየር ወለድ ጦር አዛዥና የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳሊያ ተሸላሚ ጀኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም "የአገር ጦር መሪን ስብዕና ማጉደፍ አገርን እንደማዋረድ ይቆጠራል" ይላሉ።
ከአሁኖቹ የሰራዊት መሪዎች መካከል ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በእርሳቸው ስር እንደሰለጠኑ ለአብነት አንስተው፤ ጄኔራሉ በተሰለፉባቸው ጦር ሜዳዎች ብዙ ድሎችንና ጀብዱ ያስመዘገቡ ስለመሆናቸው አብራርተዋል።
ከዚህ አንጻር በጦር መሪዎች ላይ የሚደረገው የስም ማጥፋት ከእውነታ የራቀ ተራ አሉባልታ ነው ሲሉ ነው የተናገሩት።
የቀድሞ አየር ወለድ ጦር የትምህርትና የዘመቻ መኮንን የነበሩት ኮሎኔል ታምሩ ሀይሉ በተመሳሳይ በጦር መሪዎች ላይ የሚደረገው ስም ማጥፋት መረን ከለቀቀ ጥላቻ የመነጨ ነው ይላሉ።
ድርጊቱም የሰራዊቱን ሞራል በማንኳሰስ የግል ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረግ ከንቱ ጥረት እንደሆነ አድርገው እንደሚገነዘቡትም ነው የገለጹት።
አንዳንዶቹ ዘለፋዎች ራስን አዋቂ አስመስሎ ለማቅረብ የተደረጉ ሙከራዎች መሆናቸው በግልጽ ይታወቃል ሲሉም ነው ያስረዱት።
ነገር ግን በመስዋዕትነትም ጭምር የአገር ህልውናና የህዝቦችን አብሮነት እያስቀጠለ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ክብር መስጠት እንጂ መዝለፍ ተገቢ አይደለም ብለዋል።
የትኛውም አካል በቦታው ቢቀመጥ ከዚህ የተለየ ኃላፊነት እንደሌለውም ነው የገለጹት።
ወጣቶች ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚጥሩ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም መክረዋል።
እያንዳንዱ ዜጋ ሰላምን በመጠበቅ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እውን እንዲሆኑ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
ኢዜአ በእነዚህና ሰራዊቱ ላይ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ሰራዎችን በሚመለከት ከቀድሞ ሰራዊት የአየር ወለድ ጦር መኮንኖች ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተማርያም እና ኮሎኔል ታምሩ ሀይሉ ጋር ያደረገውን ሙሉ ውይይት በቅርቡ ለህዝብ የሚያደርስ ይሆናል።