ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ዓለም አቀፍ መርሆዎች

በአብዱራህማን ናስር (ኢዜአ)

በምንኖርባት ዓለም ከውሃ ጋር የተዛመዱ ግጭቶች እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች እየጨመሩ መጥተዋል። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንዲህ ዓይነቶቹን ግጭቶችና አለመረጋጋቶች እንዲባባሱ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት መጨመር፣ የኢኮኖሚ እያደገ መምጣት፣ ለረዥም ጊዜ የሚዘልቁ የድርቅ አደጋዎች፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአየር ብክለት፣ ለልማት ሲባል የሚከናወኑ ግድቦችና የውሃ አቅጣጫ የመቀየር ጥረቶች፣ ደካማ የሆነ የውሃ ሃብት አጠቃቀምና የውሃ ብክነት፣ የተቋማት የማስፈጸም አቅም ውስንነት ይጠቀሳሉ።

በተፈጥሮ ሃብቶች አስተዳደር ዙሪያ ጥናት የሚያደርገው ወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት የተባለ ተቋም እኤአ በ2020 ባደረገው ጥናት መሰረት በ1930ዎቹ መጀመሪያ ከውሃ ጋር የተያያዙ ግጭቶች እምብዛም ያልተከሰቱ ሲሆን በ2018 የግጭት ክስተቱ በ90 በመቶ እድገት ማሳየቱን አመላክቷል። ይኸው ተቋም በ2020 ‘Ending Conflicts over Water: Solutions to Water and Security Challenges’ በሚል ርእስ ባካሄደው ጥናት ከዓለም ህዝብ አንድ አራተኛውን የሚሸፍኑ 17 ሀገሮች እጅግ ከፍተኛ የውሃ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁሟል። በተመሳሳይ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የውሃ ብክለት፣ የከፋ ድርቅ እና ጎርፍ፣ እንዲሁም ንፁህ እና ተደራሽ የሆነ የመጠጥ ውሃ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው አመልክቷል።  እነዚህ ተግዳሮቶች ለፀጥታ ችግር፣ ለስደት እና ለእርስ በርስ ግጭት የሚዳርጉ መሆናቸውን የጠቀሰው ጥናቱ በተለይ የገንዘብ፣ የቴክኒክ እና የአስተዳደር አቅም በሌላቸው በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ችግሩ የከፋ እንደሚሆን አረጋግጧል። በኢራቅ፣ የመን፣ ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ናይጄሪያ እና የመሳሰሉ አገራት እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች ከውሃ ጋር የተያያዙ ስለመሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል።

በእርግጥ ከውሃ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሁሉ የግድ ወደ ግጭት ይወስዳሉ ማለት አይደለም፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ከሆነ በማናቸውም ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሀገሮች መካከል በውሃ መስክ ጠንካራ ትብብር የሚኖር ከሆነ በጋራ የመልማት አቅማቸው ከማሳደጉም በላይ የሰላምና የወዳጅነት ትስስራቸውም ጠንካራ ይሆናል፡፡ ይህም በመሆኑ በአገራቱ መካከል በቀላሉ ወደ ግጭት የሚያመሩና ለግጭት ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ይቀንሳሉ።

በተለይ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ዓለም አቀፋዊ መርሆዎችን የተከተለና በትብብር መንፈስ ጥቅም ላይ እንዲውል ከተደረገ በጋራ የመልማት እድሎችን እንደሚያሰፋ የዘርፉ ምሀራን በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ስለሆነም አገራቱ ግጭትን ለማስወገድ ፍትሐዊና አግባብ ባለው መንገድ የሚጠቀሙበትን ስርዓት ማበጀትና ግትር አቋምን ማስወገድ እንደሚኖርባቸው ይመክራሉ፡፡

ዓለም አቀፍ መርሆዎች ምን ይላሉ?

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አንድ ሀገር በግዛቱ የሚፈሰውን የውሀ ሀብት የመጠቀም መብት እስከምን ድረስ እንደሆነና በምን መሰረታዊ የአለምአቀፍ ህግ መርሆች ላይ መሰረት እንዳደረገ የሚደነግጉ የተለያዩ የህግ ማእቀፎችን ስራ ላይ እንዲውሉ አድርጓል። የተለያዩ የጥናት ሰነዶች እንደሚያመለክቱት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አጠቃቀም በተመለከተ አምስት ዓይነት ዓለም አቀፍ መርሆች ያሉ ሲሆን፤ እነዚህ መርሆች በዓለምአቀፍ ህግ ታሪክ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በሚጣጣም መልኩ የተፈጠሩ አሊያም የከሰሙ፣ ሌሎቹ ደግሞ እየዳበሩና እየተሻሻሉ የመጡ ናቸው፡፡

ከዓለም ዓቀፍ መርሆዎች መካከል የግዛት ፍፁም ሉዓላዊነት መርህ አንዱ ነው። የዚህ መርህ ፅንሰ-ሀሳብ ሀገራት በግዛታቸው የሚፈሰውን ወንዝ ውሀ ያለገደብ በነፃነት የመጠቀም መብት እንዳላቸው ያረጋግጣል፡፡ የዚህ ፅንሰ-ሀሳብ መነሻ በአሜሪካና በሜክሲኮ መካከል በሪዮ ግራንዴ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ የተፈጠረው አለመግባባት ነው። የአሜሪካን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት ከፍተኛ ሃላፊ የነበረው ሀርሞን በአሜሪካ ኮሎራዶ ግዛት የሚገኙ ገበሬዎች የሪዮ ግራንዴ ወንዝ ውሀ ጠልፈው በመጠቀማቸው በተፋሰሱ ታችኛው ክፍል የምትገኘው ሜክሲኮ ወደ ግዛቴ የሚገባው የውሀ መጠን ቀንሷል በማለት ላቀረበችው ክስ የሰጠው የመከራከሪያ መልስ ነው፡፡

በግዛት ፍጹም ሉአላዊነት መርህ መሠረት በወንዙ ራስጌ የሚገኙ ሀገራት በግዛታቸው የሚፈሰውን ውሀ ያለምንም ገደብ የመጠቀም መብታቸው ሲረጋገጥ በአንጻሩ ደግሞ የግርጌ ሀገራት ሃብቱን ቀደም ብለው ግልጋሎት ላይ በማዋላቸው ምክንያት ብቻ ፍሰቱን በተመለከተ ሌላውን ሀገር ግዴታ ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉበት ሁኔታ የለም፡፡

ሌላኛው ዓለም አቀፍ መርህ ደግሞ ገደብ ያለው ሉዓላዊነት መርህ ሲሆን ይህ የህግ ማእቀፍ አንድ ሀገር በግዛቱ የሚያልፈውን ውሀ በሌላ ተጋሪ ሀገር ላይ ጉልህ የሆነ ጉዳት በማያስከትል መልኩ መገልገል እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ በአለም አቀፍም ሆነ በመንግስታት ሕግ መሠረት ማናቸውም ሃገር ግዛቱን ለማናቸውም አላማ በሚጠቀምበት ጊዜ ወይም ሌሎች እንዲጠቀሙ ሲፈቅድ፣ በጎረቤት አገር ግዛት ንብረትም ሆነ ነዋሪዎች ጉዳት ሊያደርስባቸው አይገባም የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡

በዚህ መርህ መሰረት ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በሚጋሩት ወንዝ ውሀ ላይ ተመጣጣኝ የሆነ ጥቅም የማግኘት መብት ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ህግ ሀገራት የሚጋሩትን ወንዝ ውሀ በፍትሐዊነትና ሚዛናዊነት እንዲገለገሉ የሚያስችላቸው ከመሆኑም ባሻገር የግዛት ፍጹም ሉአላዊነትም ሆነ ፍጹም አንድነት መርሆዎችን መሰረት በማድረግ ከሚቀርቡ መከራከሪያዎች የተሻለ መሆኑን ይነገርለታል።

በሌላ በኩል የፍትሐዊና ሚዛናዊ አጠቃቀም መርህ  ሌላኛው ሲሆን ይህምበወቅታዊ የአለምአቀፍ የውሃ ህግ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህ መርህ እጅግ በርከት ባሉ ድንበር ታሻጋሪ ወንዞች በሚመለከቱ ስምምነቶች፣ የፍርድ ቤት ግልግል ውሳኔዎች እና የአገራት ተሞክሮዎች በሰፊው ስራ ላይ የዋለ ነው፡፡ መሰረታዊ ሃሳቡም ሀገራት የሚጋሩትን የወንዝ ውሀ ፍትሐዊና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የመጠቀም እኩል መብት አላቸው የሚል ነው፡፡

ፍትሐዊና ሚዛናዊ አጠቃቀም የሁሉንም የተፋሰስ ሀገራት ፍላጎትና ጥቅም በማስጠበቅ በወንዙ ውሀ ላይ የተመጣጠነ ጥቅም እንዲኖራቸው የሚያስችል በመሆኑ መርሁ ሰፊ እውቅና የተቸረው የዓለም አቀፍ ውሀ ሕግ አንድ አካል ሲሆን፣ በሀገራት ልማዳዊ አሰራር፣ በፍርድ ውሳኔዎች እና በአለም አቀፍ ልማዳዊ ሕጎች ጠንካራ ድጋፍና ተቀባይነት ያለው ነው፡፡

የውሃ ዘርፍ የህግ ምሁራን እንደሚገልጹት ፍትሐዊና ሚዛናዊ አጠቃቀም መሠረት ያደረገው በጋራ ሉዓላዊነትና በእኩልነት አስተሳሰቦች ላይ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ሀገራት ውሀውን የግድ እኩል መከፋፈል አለባቸው ማለት አለመሆኑን አክለው ይገልጻሉ።

በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች በተጋሪ ሀገራት መካከል እንዳሉ የጋራ ሀብቶች የሚታሰቡ ሲሆን አገራቱም በእኩልነት የመጠቀም መብት እንዳላቸው የሚገልጽ ነው፤ የሕብረት ጥቅም መርህ። በአሁኑ ወቅት ባለውና ሰፊ ተቀባይነት ባገኘው የሕግ አስተምህሮት በተለያዩ ሀገራት ግዛት ውስጥ የሚገኝ ድንበር ተሻጋሪ ሀብት ለሀገራቱ የጋራ ሀብታቸው እንደሆነ የሚቆጥር ነው፡፡

ይህ ህግ ከሌሎቹ ሰፊ ተቀባይነት ካገኙ የህግ ቲዎሪዎች በተለይም ገደብ ያለው ሉዓላዊነት መርህ እና ፍትሐዊ አጠቃቀም መርህ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው መሆኑን የሚነገርለት ሲሆን አገራት የሌሎች ተጋሪ ሀገራትን ጥቅም ባገናዘበና ሚዛናዊነትን በጠበቀ መልኩ የመገልገል መብት እንዳላቸው የሚገልፅ ነው፡፡

ሌላኛው መርህ ደግሞ የግዛት ፍፁም አንድነት መርህ ሲሆን፤ የዚህ መርህ ጽንሰ ሀሳብ በወንዙ የላይኛው ተፋሰስ በኩል ያለ ሀገር በግዛቱ ውስጥ የሚያልፈውን ውሀ በሌላ ሀገር ላይ ጉዳት የሚያስከትል ማናቸውንም ዓይነት ተግባር እንዳያከናውን የሚከለክል ነው፡፡ ስለሆነም የግርጌ ተጠቃሚ ሀገር በተፈጥሮ ከሌላ ተዋሳኝ ሀገር የሚፈሰው የወንዝ ውሀ መጠኑ ሳይቀንስ ግዛቱ ውስጥ እንዲገባ የመጠየቅ መብት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም በራስ ግዛት ውስጥ የሚፈሰውንና ወደ ጎረቤት ሀገር ግዛት የሚዘልቅ የወንዝ ውሀ መጥለፍ፣ የወንዙን ውሀ በመጠቀም ጎረቤት ሀገር ላይ ጉዳት የሚያደርስና የታችኛው ተፋሰስ አገር በውሀው የመጠቀም መብትን የሚነካ ማናቸውም ድርጊት መፈጸም አይችልም፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ይህ ህግ የተፋሰሱ የላይኛው አገራት ከወንዙ ተመጣጣኝ የሆነ ጥቅም እንዳያገኙ የሚያደርግ በመሆኑ ፍትሀዊነት የጎደለውና ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም ባሻገር መርሁ በአለም አቀፍ ህግ ደረጃም ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነትን ካጡና ከቆዩ ህጎች የሚመደብ ነው፡፡  

የጋራ ተጠቃሚነት ለዘላቂ መፍትሔ ሌላኛው ዓለም ዓቀፍ መርህ ነው።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እኤአ በ2018 ለእያንዳንዳ ጠብታ ዋጋ መስጠት በሚል ርእስ ባወጣው ሰነድ ውሃን ከግጭት ነፃ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረጉ ጉዳይ ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በቀጥታ ያስተሳሰረው ሲሆን የውሃ አስተዳደር ከሃገራት የፖለቲካና ኢኮኖሚ አወቃቀር፣ ከከተሞች መስፋፋትና ከስነህዝብ ስርጭት እንዲሁም ከአደጋ ስራ አመራር ጋር አስተሳስሮታል። በዚህ መሰረት ውሃን በሚመለከት ለሚቀጥሉት 10 አመታት በፈጠራ፣ በአጋርነትና ትብብር ላይ የተመሰረቱ አለም አቀፍ ዘመቻዎች ሊተገበሩ እንደሚገባ ያመለክታል።

የተፋሰስ አገሮች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በድንበሮቻቸው ክልል አግባብ ባለውና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ ዓለም አቀፍ መርሆ እንዳለ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አግባብ ያለውና ፍትሐዊ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ውኃ አጠቃቀም ሥርዓት ከአገሮቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ የሚኖረው የውኃ ክፍል ተጨባጭ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት፣ እንዲሁም የወንዙን ውኃ ለመንከባከብ፣ ለመጠበቅ፣ ለማልማትና ውኃውን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ወሳኝ ጉዳዮች ስለመሆናቸውም ይናገራሉ፡፡

በ1997 የፀደቀ አንድ ዓለም አቀፍ ስምምነት እንደሚደነግገው ማንኛውም የተፋሰሱ አገር በሌላው አገር ጥቅም ላይ ከፍ ያለ ጉዳት እንዳያደርስ በመተሳሰብ መርህ ላይ የተመሠረተ የውኃ አጠቃቀም ሥርዓት እንዲተገብር ያስገድዳል፡፡ ኮንቬንሽኑ እያንዳንዱ የተፋሰስ አገር የጋራ በሆነው የተፈጥሮ ሀብት ዙሪያ ስለሚያከናውነው ማናቸውም የልማት ተግባር ከሌሎቹ አገሮች ጋር በየጊዜው እየተቀራረቡ ሐሳብ መለዋወጥ፣ መረጃና መግለጫ መሰጣጠት እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ አንድ የተፋሰስ አገር በወንዙ ላይ የሌላውን ተፋሰስ አገር ጥቅም ሊነካ የሚችል ዕቅድ ከመተግበሩ በፊት ቴክኒካዊ መረጃዎችን ለዚያ አገር በወቅቱ መላክ ይኖርበታል፡፡

ዎርልድ ሪሶርስስ ኢንስቲትዩት ከውሃ ጋር በተያያዘ በአገራት መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ከበርካታ አማራጮች መካከል ሶስቱን በመፍትሔነት ይጠቁማል። አንደኛው አማራጭ የውሃ ሃብት ከብክነት መከላከል ሲሆን በርካታ አገራት ውጤታማና ብቃት ያለው የውሃ አስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ ማድረጋቸውን ይጠቁማል። ሌላኛው የመፍትሔ አማራጭ ከኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ዘላቄታዊ እይታ አኳያ ጥንቃቄ የተሞላበት የውሃ ሃብት አጠቃቀም ሲሆን ይህም ለግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ውሃን እንደዋነኛ ግብአት የሚጠቀሙ ባለሃብቶች ውሃውን መልሰው እያጣሩ እንዲጠቀሙና የውሃ ብክለትንና ብክነትን ሊቀነሱ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንዲጠቀሙ አስገዳጅ መመሪያዎችንና ህጎችን መተግበር እንደሚገባ ይገልጻል። ሶስተኛው የመፍትሔ አማራጭ ከፖሊሲ እና አስተዳደራዊ መፍትሔዎች አኳያ የሚታይ ሲሆን ሰፊ መሰረት ያላቸው የውሃ ተጠቃሚዎችን በማሳተፍ የማህበረሰቦችንና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ውሳኔና ይሁንታን ያገኘ የውሀ ሀብቶች አጠቃቀምና አያያዝ ተግባራዊ ማደረግ እንደሆነ ይመክራል።

በጥቅሉ ሲታይ አገራት የመልማት ፍላጎታቸውን ለማሳካት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ከግጭት ነፃ በሆነ መልኩ የዓለም አቀፍ መርሆዎችን መሰረት ባደረገ መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል። የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ግልጋሎት ለመወሰን የወጣው የ1997ቱ የተመድ ኮንቬንሽን በጋራ መተባበርን እንደ ግዴታ ይጥላል፡፡ ስለሆነም የአገራቱ ግንኙነት በዚህ መርህ መመራት እንዳለበት አያጠራጥርም። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በትብብር መንፈስ ማስተዳደር የአፈር መሸርሸርን ለመቀነስ፣ ድርቅን ለመግታት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፤ ለኃይል ማመንጨት እና የውሃ ብክለትን ለመቆጣጠር እንዲሁም የተሻለ የውሃ አስተዳደርና ልማትን ለማምጣት ቁልፍ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በጎርፍና በድርቅ የሚመጣን አደጋ በተሻለ ደረጃ ለመቆጣጠር ያስችላል።

ግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያን የሚያስተሳስረው የዓባይ ወንዝ በአገራቱ መካከል ባለ ያልተመጣጠነ የውሃ አጠቃቀም ሳቢያ ግንኙነቱ እንዲሻክርና በውጥረት የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ኢትዮጵያ የዐባይ ወንዝ የሚመነጭባት አገር ብትሆንም ፍጹም አልተጠቀመችበትም ማለት ይቻላል። በአንፃሩ ግብጽ እና ሱዳን የዓባይን ወንዝ ለመስኖና ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ባለፈ ለቱሪስት ፍሰት ትልቅ  ጠቀማቴ አለው። በተለይ ግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን ኢትዮጵያን ሳያካትት በተፈፀመ ስምምነት ሳቢያ የዓባይ ወንዝ ከፍተኛውን የውሃ ድርሻ ተጠቃሚ ከመሆኗም በላይ የውሃውን መጠን ምንም ሳይቀንስ ወደ ግዛቷ እንዲገባ ካላት ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ኢትዮጵያ ከወንዙ እንዳትጠቀም በተለያዩ መንገዶች በመከልከል ወንዙን በባለቤትነት ተቆጣጥራ ስትገለገልበት ቆይታለች፡፡

ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዘመናት በወንዙ ላይ የወጠነቻቸውን የልማት ዕቅዶች በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ለረጅም ጊዜ ተግባራዊ ሳታደርግ ብትቆይም በአሁኑ ወቅት እያደገ ካለው የሃገሪቷ የሕዝብ ቁጥርና የልማት ፍላጎት አንፃር ወንዙን ጥቅም ላይ ማዋል አማራጭ የሌለው ጉዳይ በሆነበት ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ በግዛቷ በሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ሙሉ መብት እንዳላት ሁሉ በግዛቷ በሚፈስው የዓባይ ወንዝ የውሀ ሀብት ላይም ተመሳሳይ መብት አላት። ወንዙን በአለም አቀፍ የተፋሰስ ሕግ መሠረት ፍትሐዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም መብቷም የተጠበቀ ነው። በመሆኑም ግብጽ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን የፍትሐዊና ሚዛናዊ አጠቃቀም መርህን በመከተል የዐባይን ወንዝ ለግጭት ሳይሆን ለጋራ ልማት ጥቅም ላይ ሊያውሉት ይገባል፤ ይቻላልም።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም