ምርምር ማዕከሉ 253 ኩንታል የተሻሻለ የቡና ዘር ለተጠቃሚዎች አሰራጨ - ኢዜአ አማርኛ
ምርምር ማዕከሉ 253 ኩንታል የተሻሻለ የቡና ዘር ለተጠቃሚዎች አሰራጨ
ጅማ፣መስከረም 29/2013 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት አመት 253 ኩንታል የተሻሻለ የቡና ዘር ለተጠቃሚዎች ማሰራጨቱን የጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ግርማ ኃይለሚካኤል የቡና ዘሩ የአካባቢን አየር ጠባይ መሰረት በማድረግ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተጠቃሚዎች ተሰራጭቷል።
ቡና አምራች ለሆኑ አርሶ አደሮች፣ ባለሀብቶችና ተቋማት መሰራጨቱን ጠቅሰዋል።
የተሰራጨው ዘር 25 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚችል መሆኑን ተናግረዋል ።
ማዕከሉ ከዚህ ቀደም በምርምር ያወጣቸውን በሽታ የሚቋቋሙ፣ ፈጥነው የሚደርሱና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ዘር በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል ።
በተለይ በምርምር የተገኙ የዲቃላ ቡና ዝርያዎች በሄክታር እስከ 26 ኩንታል ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋ።
ማዕከሉ ከዘር በተጨማሪ የቡና ተክል የአሰራር መመሪያ አዘጋጅቶ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ ማድረጉን ተናግረዋል
መመሪያው ከዝርያ መረጣ ጀምሮ እስክ ድህረ ምርት ባለው ሂደት ጥራቱን የተጠበቅ ቡና አምርቶና አዘጋጅቶ ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል ።
በጅማ ዞን በሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ቀመር የሰፉ ከማዕከሉ የወጡ ምርጥ የቡና ዝርያዎች በተተከሉ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ የምስራች ፍሬ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ነባሩ የቡና ዝርያ የምስራች ፍሬ ለመስጠት ከአራት አመት በላይ እንደሚፈጅበት አስታውሰዋል።
"በማእከሉ የተዘጋጀ የቡና አተካከል መመሪያ ተከትዬ በመስራቴና ውጤታማ በመሆኔ እውቅናና የምርት መሳሪያ ሽልማት ተሰጥቶኛል" ብለዋል።