ቀጥታ፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኖቤል ሰላም ሽልማትን አሸፈ

አዲስ አበባ፣መስከረም 29/2013 (ኢዜአ) የዓለም ምግብ ፕሮግራም የዚህን ዓመት የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸነፈ።

በዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት 211 ግለሰቦች 107 ተቋማት 318 ዕጩዎች  የቀረቡ ሲሆን፣ ከአራት ዓመታት በፊት ለሽልማቱ ከተወዳደሩት 376 ዕጩዎች በመቀጠል በርካታ ዕጩዎች እንደተወዳደሩበት ተገልጿል።

ፕሮግራሙ  የአውሮፓውኑ የ2020 ሽልማትን ያሸነፈው ረሃብን በመዋጋት ባደረገው ጥረት ፣ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ረሃብ የጦርነትና ግጭት መሳሪያ እንዳይሆን ባበረከተው አስተዋጽኦ መሆኑን የኖቤል የሰላም ኮሚቴ ሊቀመንበር ቤሪት ሪይስ-አንድርሰን ዛሬ አስታውቀዋል።

ሽልማቱ የዓለም ዓይኖች በ88 አገሮች በሚገኙ 100 ሚሊዮን ገደማ በምግብ ዋስትና አለመረጋገጥና በረሃብ ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን እንዲመለከቱ ያደርጋል የሚል ተስፋ አለኝ ብለዋል ሊቀመንበሯ።

ፕሮግራሙ  ዓለም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ውስጥ ሆና አቅሙን በማሳደግ እያከናወነ ያለውን ተግባር  አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ጦርነቶችና ግጭቶችን ካላስቆምን ከዓለም ላይ ረሃብን ለማጥፋት ያስቀመጥነውን ግብ ማሳካት የማይታሰብ ነው ያሉት ሊቀመንበሯ፣ ይህም ትብብርንና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል ብለዋል።

ሽልማቱን ለ101ኛ ጊዜ ያሸነፈው የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሽልማቱን "በጣም የሚያኮራና የሚያስደስት" ሲል ገልጾታል።

የፕሮግራሙ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሌይ ለአሶሴትድ ፕሬስ ዜና አገልግሎት ''በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ቃላት አጠሩኝ'' በማለት  ድርጅታቸው በማሸነፉ የተሰማቸውን ስሜት ገልጸዋል።

የዓለም የጤና ድርጅትና ስዊድናዊቷ  የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች ግሬታ ቱንበርግ የዘንድሮውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ያገኛሉ ተብሎ የቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው ዕጩዎች መካከል ነበሩበት።

ፕሮግራሙ ሽልማቱን በማሸነፉ የ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኝ ሲሆን፣የኖቤል ዲፕሎማና የኖቤል ሜዳሊያም ይቀበላል።

ሽልማቱ ታህሳስ 1 ቀን 2013 በኖርዌይ መዲና ኦስሎ በሚካሄድ ሥነ ሥርዓት  ይሰጣል።

ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶክተር ዐቢይ አህመድ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በተለይም ከኤርትራ ጋር ለተፈረመው የሰላም ስምምነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ያለፈው ዓመት የኖቤል የሰላም ተሸላሚ መሆናቸው ይታወሳል።

ዓለም አቀፉ የህጻናት መርጃ ድርጅት(ዪኒሴፍ) እ.አ.አ በ1965 ፣  በ1981 የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ(ዩ ኤን ኤቺ ሲ አር)ና እ.አ.አ በ1998 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል ተሸላሚዎች ነበሩ።

በተጨማሪም እ.አ.አ በ2001 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ኮፊ አናን ሽልማቱን ተቀብለዋል።

የዘንድሮው የኖቤል ሽልማት  እስካሁን በሕክምና፣በኬሚስትሪ፣በፊዚክስና በሥነ ጽሁፍ አሸናፊዎች ታውቀዋል።

የኢኮኖሚ ዘርፍ አሸናፊ ጥቅምት 2 ቀን 2013 በስዊድን መዲና ስቶክሆልም ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም