የግብርና ናሙና ጥናት ግብዓት የሚሆን መረጃ ማሰባሰብ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ናሙና ጥናት ግብዓት የሚሆን መረጃ ማሰባሰብ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣መስከረም 29/2013 (ኢዜአ) የግብርና ናሙና ጥናት ግብዓት የሚሆን መረጃ ማሰባሰብ መጀመሩን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ገለጸ።
የግብርናውን ዘርፍ መረጃ ፍላጎት ለማልማት በየዓመቱ ከመስከረም 1 እስከ ግንቦት 30 ድረስ መረጃ የሚያሰባስበው ኤጀንሲው፤ የ2013 ዓ.ም ግብርና ናሙና ጥናት መጀመሩን በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
ናሙና ጥናቱ ከሚዳስሳቸው ጉዳዮች መካከል የምርት እድገት፣ መሬት አጠቃቀምና እርሻ አስተዳደር፣ የቤት እንስሳት ብዛት፣ አይነት፣ እድሜና ጾታ እንዲሁም የአገልግሎት ተዋጽኦ ይገኙበታል።
ከዚህ ባለፈም የደረቅ ወቅት መስኖ የእርሻ ሁኔታ፣ የበልግ ወቅት የእርሻ ሁኔታ የሰፋፊና መካከለኛ የንግድ እርሻ ሁኔታ፣ የዓሣ ኃብት፣ የሰብልና እንስሳት ተዋጽኦ እና የቅድመና ድህረ ሰብል ብክነት ጥናት ይካሄድባቸዋል።
የኤጀንሲው ህዝብ ግንኙነትና መረጃ ስርጭት ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ እንደተናገሩት፤ ከዚህ በፊት እንደሚደረገው በ2013 ዓ.ም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ናሙና ጥናት ተጀምሯል።
በጥናቱ የመረጃ ጥራትና ወቅታዊነት ትኩረት መሰጠቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ መረጃ የሚሰባሰብበት ዘዴ፣ መጠይቅና ዘመናዊ ዲጂታል መረጃ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
በጥናቱ ላይ የሚሳተፈውን የሰው ኃይል በመመልመልና በቂ ስልጠና በመስጠት ስራው መጀመሩን ያብራሩት ዳይሬክተሩ፤ ''ጥናቱ የሚካሄደው በናሙና ከተመረጡ 2 ሺህ 769 የቆጠራ ቦታዎች ውስጥ 55 ሺህ 380 አነስተኛ የግብርና የግል ባለይዞታዎች ላይ ነው'' ብለዋል።
261 የስታትስቲክስ ባለሙያዎች፣ 705 የመስክ ተቆጣጣሪዎችና 2 ሺህ 420 መረጃ ሰብሳቢዎች በጥናቱ እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።
በሰፋፊና ንግድ እርሻ ናሙና ጥናት ላይ ደግሞ ከ3 ሺህ 455 እርሻ አልሚዎች በመጠይቅ መረጃ የሚሰበሰብ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሳፊ፤ 25 የስታትስቲክስ ባለሙያዎች፣ 42 የመስክ ተቆጣጣሪዎችና 131 መረጃ ሰብሳቢዎች እንደሚሳተፉበት ጠቅሰዋል።
በጥናቱ የሚገኘው ውጤት በግብርናው የሚመረተው ምርት በቂ መሆኑን ለማወቅና የግብርናው መስክ ለአገሪቷ ኢኮኖሚ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ለማወቅ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
ከግብይት አንጻርም በባለኃብቶች የሚፈልግ ምርት መኖሩን ለመለየት እንደሚያግዝም አስረድተዋል።
እንደ አቶ ሳፊ ገለጻ፤ የናሙና ጥናት ውጤቱ ለመንግሥትና ለምርምር ተቋማት በግብዓትነት ያገለግላል።
በኤጀንሲው የግብርና ከባቢና ተፈጥሮ ኃብት ዳይሬክተር አቶ አህመድ ኢብራሂም የናሙና ጥናቱ አርሶ አደሩ ለማምረት የተጠቀመባቸውን መሳሪያዎች ምንነት፣ ካመረተው ምን ያህሉን ለገበያ እንዳቀረበ እና ምን ያህሉን ለራሱ እንዳዋለ ከግምት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የአንበጣ መንጋ ያለውን ተጽእኖ ለማወቅም ሰፋ ያለ መጠይቅ ተዘጋጅቶ መረጃ እንደሚሰበሰብ አክለዋል።
የናሙና ጥናቱ ሲጠናቀቅ የሚገኘው ውጤት በተቋሙ ድረ ገጽና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በኩል ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።