ቀጥታ፡

በህገ መንግስቱ የሰፈሩት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት ላለፉት ዓመታት በአግባቡ ሲተገበሩ አልነበረም---አፈ ጉባኤዎች

አዲስ አበባ፣መስከረም 29/2013 (ኢዜአ) በህገ መንግስቱ የሰፈሩት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት ላለፉት ዓመታት በአግባቡ ሲተገበሩ እንዳልነበር የክልልና የከተማ አስተዳደር አፈ ጉባኤዎች ተናገሩ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ማግስት በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩት የፌደራሊዝም ስርዓትና የማንነት መብቶችን ተግባራዊ በማድረግ በኩል የተሻለ ለውጥ መምጣቱንም ገልጸዋል።

አፈ ጉባኤዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት ኢህአዴግ መንበሩን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት እንዲከበር የራሱ የሆነ ሚና ተጫውቷል።

ከለውጥ በፊት የፌደራሊዝም ስረዓት እንዲጀመር፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በባህላቸውና በቋንቋቸው እንዲጠቀሙ የማድረግ ጅምሮች እንደነበሩም አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ እውነተኛ ፌደራሊዝም ከመተግበር፣ በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መብት በማረጋገጥ ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ግን በርካታ ውስንነቶች እንደነበሩበት ተናግረዋል።

የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ተከበረ የሚባለው የማንነት ጥያቄዎችን በአግባቡ ማስተናገድ ሲቻል እንደሆነ የገለጹት አፈ ጉበኤዎቹ በላፉት ዓመታት የማንነት ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ እንኳን ማቅረብ የማይቻልበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል።

በተለይ ለፌደራሊዝም ስርዓትና ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት መከበር ወሳኝ የሆኑ የማንነት ጥያቄዎች እንዲሁም ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች የታፈኑበትና የጠየቁ አካላትም በህገ ወጥነት የሚታሰሩበት ጊዜ እንደነበር ተናግረዋል።

የነዚህ መብቶች አለመከበር አሁን ያለውን ለውጥ ማምጣቱን የገለጹት አፈ ጉባኤዎቹ፣ ቀጣዩ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል የሚከበረው እነዚህ ጉድለቶች ታርመው መሆኑን ተናግረዋል።

"ከለውጥ በኋላ ያለው መንግስት አሃዳዊ ነው፣ ፌደራሊዝም ስርዓቱን አፍርሷል የሚሉ አሁን ካለው እውነታ የራቀ አመለካከት ያላቸው ናቸው" ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ትክክለኛ ፌዴራሊዝም ለመኖሩ ራሳቸውን እንደማሳያ የገለጹት የሲዳማ ክልልና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አፈ ጉባኤዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትና እወነተኛ ፌደራሊዝም በትክክል የሚተገበረው ህገ መንግስቱን ማክበር ሲቻል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህንን ለማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቅርቡ የወሰናቸው ውሳኔዎች ህገ መንግስቱን የሚያስከብሩ መሆኑን ገልጸው የፌደራልና የክልል መንግስታት ውሳኔው ተግባራዊ እንዲሆን ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ውሳኔው የጋራ መሆኑንና በአፈፃፀሙም ላይ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅ የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም